ለአማራ ክልል መልሶ ማቋቋምና ግንባታ የሚውል የድጋፍ ስምምነት ተደረገ።

0
108

ባሕር ዳር: ሰኔ 20/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ በክልሉ ለመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ድጋፍ የሚኾን 6 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር የእርዳታ ስምምነት ፕሮጀክት ከተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ጋር አድርጓል።
ስምምነቱን የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ኃላፊ ጥላሁን መሐሪ (ዶ.ር) እና በተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ዋና ተጠሪ ሚስተር ቱርሃን ሳለህ ተፈራርመዋል።
ዶክተር ጥላሁን የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት በክልል ደረጃ ወደ አማራ ክልል ገብቶ የልማት ድጋፍ ሲያደርግ የመጀመሪያው መኾኑን ገልጸዋል። ድጋፉ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ በመገንባት በኩል የክልሉን ሥራ የሚያግዝ እንደኾነም ተናግረዋል።
ዶክተር ጥላሁን አማራ ክልል የደረሰውን ውድመት በክልሉ አቅም ብቻ መልሶ ለማቋቋም አስቸጋሪ በመኾኑ ሌሎች ረጅ ድርጅቶችም ተባባሪ እንዲኾኑ ጥሪ አቅርበዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት የክልሉን ጉዳት ተረድቶ ለመደገፍ በመምጣቱ ዶክተር ጥላሁን ምስጋና አቅርበዋል።
የልማት ድርጅቱ ዋና ተጠሪ ቱርሃን ሳለህ በበኩላቸው በአማራ ክልል በጦርነት ምክንያት ብዙ የሕዝብ መገልገያ መሰረተ ልማቶች መውደማቸውን እንደተገነዘቡ ገልጸዋል። ይኽንን መልሶ ለመገንባትና ለሕዝብ አገልግሎት ለማዋልም የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት ከአማራ ክልል መንግሥት ጋር በመተባበር ይሠራል ብለዋል።
ቱርሃን በአማራ ክልል በጦርነት ውስጥ በነበሩ ዞኖች የሚገኙ ሴክተር መስሪያ ቤቶች፣ የጤና ተቋማ እንዲሁም የፍትሕና የፀጥታ ተቋማት ወድመዋል ብለዋል። የፍትሕ ተቋማትን ሥራ በመደገፍ ክልሉ ሰላሙ የተረጋገጠ እንዲኾን በጋራ እንደሚሠሩም ነው ያስገነዘቡት።
ቱርሃን በጦርነት ምክንያት አነስተኛ የንግድ ሥራቸው የተቋረጠባቸውና ሥራ አጥ የኾኑ ዜጎችን እንደሚደግፉም ተናግረዋል።
ዛሬ የተደረገው ድጋፍም 14 የመስክ ተሽከርካሪ፣ ጥሬ ገንዘብ እና ላፕቶፕ ኮምፒውተሮች የተካተቱበት ነው። አጠቃላይ የድጋፉ ስምምነት መጠኑም በገንዘብ ሲተመን 6 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር እንደኾነ ተገልጿል።
ዘጋቢ:–አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/