ለተፈናቃዮች የሚደረገው እርዳታ ቀጥሏል፡፡

0
67

ስኩል ሚል ኢኒሼቲቭና ጅግዳን ኮሌጅ በአማራ ክልል ተፈናቅለዉ በመጠለያ ላሉ ዜጎች የተመጣጠነ የአልሚ ምግብና በቆሎ ድጋፍ አበረከቱ፡፡

Image may contain: one or more people

ባሕር ዳር፡ የካቲት 21/2011 ዓ.ም(አብመድ) ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በአማራ ክልል ለሚገኙ ወገኖች ድጋፉ ቀጥሏል፡፡

የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኘሮግራም ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የዓይነት ድጋፎቹን ተረክቧል።

ስኩል ሚል ኢኒሸቲቭ 200 ኩንታል የተመጣጠነ ምግብ ለተማሪዎች ምገባ አገልግሎት እንዲዉል ሰጥቷል። በገንዘብ ሲተመን 504 ሺህ ብር እንደሚገመት ተነግሯል። ከመንግሥት ጋር በመተባበር በዋግኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን መቀንጨርን ለመከላከል በወይዘሮ ፍሬአለም ሽባባዉ የተመሠረተዉ ስኩል ሚል ኢንሼቲቭ የሕጻናት ምገባም ያካሂዳል።

ጅግዳን ኮሌጅ ደግሞ 300 ኩንታል በቆሎ ለተፈናቃዮች ረድቷል፤ ይህም 215 ሺህ ብር በገንዘብ የተገመተ ነዉ። ጅግዳንም ከዚህ በፊት ለተፈናቃዮች 500 የቤት ክዳን ቆርቆሮና የበሰለ ምግብ ድጋፍ ማድረጉ ተገልጧል።

እስከዛሬ ድረስ ለተፈናቃዮች 45 ሚሊዮን ብር በገንዘብ ድጋፍ መደረጉ ታውቋል። የዓይነት ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኘሮግራም ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት አሳዉቋል።

ዛሬ ከተደረገው ድጋፍ 200 ኩንታሉ ፍኖተሰላም ከተማ እና 100 ኩንታል በቆሎ ደግሞ ቻግኒ ከተማ በጊዜያዊ መጠለያ ዉስጥ ላሉ ተፈናቃዮች ይበረከታል።

ከ90 ሺህ በላይ ወገኖች ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በአማራ ክልል ውስጥ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡

ዘጋቢ፡- ኪሩቤል ተሾመ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here