“ለቃሉ የሚያድር መሪ የሕዝቡን ልብ ይገዛል፤ በአንድ ጥሪም ይደማመጣል”” የታሪክ ምሁር አሰፋ ባልቻ (ዶ.ር)

33

“ለቃሉ የሚያድር መሪ የሕዝቡን ልብ ይገዛል፤ በአንድ ጥሪም ይደማመጣል”” የታሪክ ምሁር አሰፋ ባልቻ (ዶ.ር)

ባሕር ዳር:የካቲት 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያውያን ከሌሎች የዓለም ጭቁን ጥቁር ሕዝቦች ቀድመው ነቅተው በክንዳቸው የጻፏት የአሸናፊነት በኩረ- ታሪክ ናት ዓድዋ። ዓለም በነጮች የበላይነት እጅ ወድቃ በአድሎ ስትማቅቅ፣ በወቅቱ የኢትዮጵያ ንቁ መሪዎች እና በሚመሩት ሕዝብ እምቢ ባይነት የእኩልነትን መንፈስ ይዛ የመጣች የታሪክ ክስተት እና እውነት ናት ዓድዋ።

ዓድዋ በኢትዮጵያዊያን የሕብረት ክንድ ሰበብ ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የወጣች የነጻነት ጮራ ናት። የዓድዋ ጦርነት ድል ለድሉ ባለቤት ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይኾን ለመላው አፍሪካውያን እና በዓለም ለሚኖሩ ጥቁሮች ሁሉ ጉልህ ቱሩፋቶችን አስገኝቷል።

በዓድዋ ድል ከተገኙ ቱሩፋቶች የአሁኑ እና መጭውም ትውልድ ምን መማር እንዳለበት በማንሳት አሚኮ ኦንላይን ከታሪኩ ምሁሩ እና የቀድሞው የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አሰፋ ባልቻ (ዶ.ር) ጋር ቆይታ አድርጓል።

እንደ ዶክተር አሰፋ ገለጻ የዓድዋ ድል ለኢትዮጽያዊያን በርካታ ጥቅሞችን አስገኝቷል። የአሸናፊነት ስነ ልቦና፣ ከድል የመነጨ ጀግንነት፣ በዓለም አደባባይ በኩራት የሚያራምድ ክብር፣ ነጻነት ፣እኩልነት፣ አይበገሬነት እና ሌሎችም ዘመን የማይሽራቸው ዓድዋ የገለጣቸው ቱሩፋቶች ናቸው ብለዋል።

ዶክተር አሰፋ የዓድዋ ድል ባለቤቶች ኢትዮጵያዊያን ይሁኑ እንጅ ድሉ ለመላው የጥቁር ዘሮች በሙሉ ነጻነትን ያቀዳጀ እንደነበር ተናግረዋል። የዓድዋ ድል ነጭን ጥቁር ማሸነፍ ቀርቶ መሞከር በማይታሰብበት በዚያ ዘመን፤ የወቅቱ የኢትዮጵያ መሪዎች ግን የይቻላል መንፈስን ሰንቀው እና ሕዝባቸውን አነቃንቀው የዓለምን ታሪክ የቀየሩበት ነው ሲሉም ዶክተር አሰፋ ተናግረዋል።

ይህ ሊኾን የቻለው ጠንካራ የኾነ አንድነት፣ መደማመጥ እና የጋራ ሀገራዊ አጀንዳ በመኖሩ እንደኾነም አብራርተዋል። ሕዝብን ለተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች በጋራ ለማንቀሳቀስ መሪዎች ሕዝባቸውን የሚያከብሩ፤ ለቃላቸውም የሚያድሩ መኾንን ይጠይቃል ሲሉ የታሪክ ምሁሩ ገልጸዋል።

“ዓድዋ ለቃላቸው የሚያድሩ እውነተኛ መሪዎች ሕዝባቸውን በአንድ ጥሪ ማሰባሰብ እንደሚችሉ የምንማርበት ታሪክ ነው” ብለዋል። “ለቃሉ የሚያድር መሪ የሕዝቡን ልብ ይገዛል፤ በአንድ ጥሪም ይደማመጣል” ያሉት የታሪክ ምሁሩ የዓድዋ ድል ለኢትዮጵያ መሪዎች ሁሉ ትልቅ ትምህርት ስለመኾኑ አብራርተዋል።

ኢትዮጵያዊያን የዓድዋን ድል የተጎናጸፉት ያደረ ቂምና ቁርሾ ይዘው በመቆዘም እና በተቃርኖ በመቆም ሳይኾን ከዳር ዳር ሆ ብለው በአንድነት ተነስተው ያስመዘገቡት አንጸባራቂ ድል ነው። ዶክተር አሰፋ የዚህ ዘመን ትውልድ ከዓድዋው ዘመን ትውልድ በርካታ ጉዳዮችን መማር አለበት ይላሉ።

ልዩነትን አስወግዶ በሕብረት መቆም የሁሉም ዓይነት ችግሮቻችን መፍትሄ ስለመኾኑም ገልጸዋል። “በዚህ ዘመንም ኢትዮጵያዊያንን በመነጣጠል ኢትዮጵያን ለመበተን የሚተጉ ጠላቶች እንደቀጠሉ ናቸው” ያሉት የታሪክ ምሁሩ ለጠላት ሴራ ተገዥ ከመኾን መቆጠብ አለብን ብለዋል። ለዚህም ከብሄር፣ ጎሳ እና ጎጥ እሳቤ ወጥቶ ኢትዮጵያን በልቡ ያነገሠ መሪ እና ሕዝብ መኾን ያስፈልጋል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ፡- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
ዲስከቨር አማራ አሚኮ https://www.facebook.com/DiscoverAmharaAMECO
አሚኮ ስፖርት https://www.facebook.com/AMECOSport
አሚኮ እውነታ ማጣሪያ https://www.facebook.com/AMECOFactCheck