ለቀጣናዊ ትብብር ዕድል የነፈገው ውጥረት የማይለየው የአፍሪካ ቀንድ ጉዳይ

466

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 15/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ተፈጥሮ ያላደለችው የተፈጥሮ ሃብት ክምችት የለም፡፡ የባሕር በር፣ ማዕድን፣ መልክዓ ምድር፣ ዘመን ተሻጋሪ ታሪክ፣ ቱባ ባሕል፣ በቂ የከርሰ ምድርና የገጸ ምድር ውኃ እና ስብጥር ያለው የአየር ንብረት ከአፍሪካ ቀንድ ጸጋዎች መካከል ውስኖቹ ናቸው፡፡

ሉዓላዊነት በነገሰበት አኹናዊው የዓለም ነባራዊ ኹኔታ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና የመስተጋብሩ ሰጭ እንጂ ተቀባይ የሚኾንበት ዘርፍ አልነበረም፡፡ ዳሩ ግን ቀጣናው ያለውን ኹሉ ሲነጠቅ ኖሯልና ዛሬም የሀገራቱ ዜጎች የምዕራባዊያንን እጅ እና ዳረጎት ጠባቂዎች ናቸው፡፡ የከበሩ የተፈጥሮ ሃብቶቻቸውን ተዘርፈው የተቀቀለ ስንዴ የሚቀበሉት የቀጣናው ዜጎች በምዕራባዊያን ተንኮል “መርፌ ውጠው ማረሻ የሚተፉ” መከረኞች ኾነዋል፡፡

የቀንዱ ተፈጥሯዊ ጸጋዎች የምዕራባዊያንን ትኩረት እና ዕይታ የሳቡት ደግሞ በቅርቡ ሳይኾን ገና በዓለም ታሪክ ማለዳ ነበር፡፡ የቀድሞ ምዕራባዊ ሀገር አሳሾችን፣ የህቡዕ መልዕክተኞችን እና ጎብኝዎችን ታሪክ ትተን በሃይማኖት፣ በትምሕርት እና በዲፕሎማሲ ሥም የገቡትን ልዑካን ብናስብ ስለትኩረታቸው እና ሴረኝነታቸው በቂ መረጃዎችን ማግኘት እንችላለን፡፡

በ1800 (እ.አ.አ) የአውሮፓ ሀገራት መንግሥታት ለሕዝባቸው እድገት የሚጠቅማቸውን ሃብት ለመቀራመት ይችሉ ዘንድ አፍሪካን ቅኝ ለመግዛት በጀርመን በርሊን ተሰባሰቡ፡፡ ተሰብሳቢዎቹ ከፊት ለፊታቸው የዓለም ካርታን ዘርግተው የአፍሪካን መሬት ተቀራመቱት፡፡ እንዳለመታደል ኾኖ ቀንዱም በዋናነት በእንግሊዝ እና ጣሊያን መዳፍ ውስጥ ወደቀ፡፡

አፍሪካዊያን በመራር ትግላቸው ከምዕራባዊያን አስገባሪዎች ነጻ ቢወጡም ትተውት ያለፉት ዳፋ ግን አኹንም ድረስ የሚጸዳ ኾኖ አልተገኘም፡፡ በተለይም እንግሊዝ ከቅኝ ግዛቷ ባለፈ የጎነጎነችው የሴራ ፖለቲካ ለመከረኛው ቀንድ ቋጠሮው እስካሁንም ድረስ አልተፈታም፡፡

ከድህረ ቅኝ ግዛት ወረራ በኋላ የአውሮፓ ሀገራትን እግር በእግር ተከትላ የገባችው አሜሪካም ለአፍሪካ በተለይም ለቀጣናው የጎን ውጋት ኾና ቆይታለች፡፡ ሰብዓዊ ድጋፍ መቸር፣ ዴሞክራሲን ማስተዋወቅ እና ሰብዓዊ መብትን ማስከበር አሜሪካ በአፍሪካ አህጉር ሀገራት ላይ ጣልቃ የምትገባባቸው መሳሪያዎች ናቸው፡፡

ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ሽብርተኛው ትህነግን የመሰለ ጉዳይ አስፈጻሚ በቀንዱ አካባቢ የሰየመችው አሜሪካ የቀጣናውን ሀገራት ተፈጥሯዊ ትስስር እና የጋራ ትብብር ወደ ፍጹማዊ መለያየት ቀየረችው፡፡ ይኽ ሁሉ የሚኾነው ግን ሀገራቱ ከትብብር ሊያገኙት የሚችሉት ጥቅም ጠፍቷቸው ሳይኾን የአሜሪካዊያንን እና የምዕራባዊያንን ጥቅም ለማስከበር ሲባል ሴራ ተሰርቶባቸው ነው፡፡

ከዚህ ላይ ግን የትኛውም የቀጣናው ሀገራት ዜጎች ልብ ሊሉት የሚገባው ምዕራባዊያን ስትራቴጂካል ከባቢ ሲሉ የሚጠሩት ቀይ ባሕር የሚገኘው በቀንዱ ውስጥ መኾኑን ነው፡፡ ምዕራባዊያን በውጭ ጉዳይ ስትራቴጂያቸው ብሔራዊ ጥቅሞቻቸውን ከሚያስከብሩባቸው አካባቢ ቀይ ባሕር ትክ የለውም፡፡

ይህንን የምዕራባዊያን የቀይ ባሕር ስትራቴጂያዊ ጥቅም በማስከበር በኩል ሽብርተኛው ትህነግን የመሰለ ጉዳይ አስፈጻሚ ላለፉት 40 በላይ ዓመታት አልታየም፡፡ ለዛም ነው ሽብርተኛው ትህነግ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ተገፍቶ ወደ መቀሌ ሲመሽግ እና ኢትዮጵያን ሲወጋ በግልጽ ከጎኑ የቆሙት፡፡

የቀድሞው የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሙሐመድ ፋርማጆ፣ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ቅርርብ አሜሪካ ከባቢውን ልዩ ትኩረት እድትሰጠው አደረጋት፡፡ የቀንዱ ሀገራት ሰብሳቢ ያለቻትን ኢትዮጵያን የማዳከሙ ሥራ እረፍት አልባ ኾነው ቀረቡ፡፡ ለጣልቃ መግቢያቸው ቀዳዳ እና ለማዳከሚያቸው መሳሪያ ደግሞ ከሥልጣን የተወገደው አሸባሪው ትህነግ እና ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተገኙ፡፡

ላለፉት ሁለት ዓመታ የሽብር ቡድኑ ትህነግ በኢትዮጵያ ላይ የፈጠረው የሕልውና አደጋ ለአሜሪካ እና ምዕራባዊያን የቀንዱ ሀገራት ትብብር ስጋት እረፍት ሰጥቷቸው ቆይቷል፡፡ ሀገራቱን በማስተባበር ቀጣናውን እስከ ምጣኔ ሃብታዊ ውህደት ለማሻገር ጥረት ላይ የነበረችው ኢትዮጵያ በውስጥ ጉዳዮቿ ስትወጠር በሀገራቱ መካከል የታየው ትብብር እና ቅርርብ የጅማሮውን ያክል የደመቀ አልነበረም፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የቀድሞው የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሙሐመድ ፋርማጆ ከሥልጣን መውረዳቸውን ተከትሎ ወደ ሥልጣን የመጡት አዲሱ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ሞሀሙድ እግራቸው ወደ ቤተመንግሥቱ ከመድረሱ አዳዲስ ለውጦችን እያሳዩ ነው፡፡ እንደ አውሮፓዊያኑ የዘመን ቀመር ከ2012 እስከ 2014 ሶማሊያን በፕሬዚዳንትነት የመሩት ሀሰን ሼክ ሞሀሙድ በሀገሪቱ ምክር ቤት ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት ሶማሊያን በርእሰ ብሔርነት እንዲመሩ መርጧቸዋል፡፡

አዲሱ ፕሬዚዳንት በቀድሞው ፕሬዚዳንት ሙሐመድ ፋርማጆ ዘመን የሶማሊያ በር ገርበብ ተደርጎባት የነበረችውን አሜሪካን ሙሉ በሙሉ ከፍተው “እምቦሳ አሰሪ” ብለዋታል፡፡ በተመረጡ ማግስት የፕሬዚዳንት ባይደን አስተዳደር አሜሪካ ጦሯን ወደ ሶማሊያ ለመላክ መወሰኗን ይፋ ሲያደርግ ከሁሉ ቀድመው “አበጀሽ” ያሉት ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ሞሀሙድ ነበሩ፡፡ ይህ የሁለቱ ሀገራት ትስስር ቀድሞውኑ የታሰበበት ካልሆነ እንዴት በአንድ ጀምበር ተሳካ ማለት ግን ለቀጣናው ሀገራት ዜጎች ወቅታዊ ጥያቄ ነው፡፡

የኾነው ኾኖ ላለፉት ሁለት ዓመታት ቀዝቀዝ ብሎ የቆየው እና በቀጣናው ሀገር ዜጎች ዘንድ ተስፋ ሰንቆ የነበረው የሦስቱ ሀገራት ትብብር በአዲሱ ፕሬዚዳንት ይቀጥል ይሆን? የአሜሪካ ጦር ወደ ሶማሊያ መግባቱ የቀጣናውን ሀገራት ግንኙነት በቅርብ ርቀት ለመከታተል ያለመ ይኾን? ለውጭ ኅይሎች ጣልቃ ገብነት ቁብ የሌላቸው እና ማዕቀብ ተብሎ ነገር የማያስደነግጣቸው የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ከአሜሪካ ጋር ለጀመሩት መልካም ግንኙነት ምን ዓይነት ዕይታ ይኖራቸው ይኾን?

ከሁሉም በላይ ግን የቀንዱ ሀገራት የትብብር ተስፋ ወደ ተሻለ ደረጃ ይደርሳል ወይስ ዳግም በውጭ ኀይሎች ሴራ ይበታተናል ለሚለው ስጋት ጊዜ ምላሽ ይኖረዋል፡፡ እስከዚያው ግን ውጥረት የማይለየው የአፍሪካ ቀንድ አኹንም ከሴራ ፖለቲካ እንዳላመለጠ ግልጽ ነው፡፡

በታዘብ አራጋው

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/