ለሰላማዊ መማር ማስተማር መምህራን የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ፡፡

0
287

ባሕር ዳር፡ መስከረም 26/2012 ዓ/ም (አብመድ) የዓለም የመምህራን ቀን በአማራ ክልል ከሚገኙ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ መምህራን በተገኙበት በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ እየተከበረ ነው::

ከመምህራን ማኅበራት እና ከትምህርት ሚኒስቴርም ታዳሚዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ፕሬዝዳንት ዮሐንስ በንቲ (ዶክተር) የመምህርነት ሙያ ታላቅ ክብር ያለው ሙያ ነው ብለዋል:: የመምህርነት ሙያ ሚናው ከፍ እንዲል እና ብቁ ዜጋ ለማፍራት እንዲቻል ወጣት መምህራን ወደ ሙያው መቀላቀል እንዳለባቸውም ነው ዶክተር ዮሐንስ የተናገሩት:: የመምህርነት ሙያ የሚከበረው በጋራ በመስራት ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ መምህራን የትውልድ ቀረፃ ተግባራቸውን በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት፡፡

በውይይቱ የታደሙት የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር ተወካይ ወይዘሮ አሰፋሽ ተካልኝ የመምህራን ሚና በገንዘብ ክፍያ የማይተካ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም በሰው ልማት ላይ የሚያከናውኑትን ሥራ በትኩረት ማስቀጠል ይገባቸዋል ነው ያሉት፡፡ በያዝነው የትምህርት ዘመን በሁሉም ደረጃ ባሉ የትምህርት ተቋማት ሰላማዊ የመማር ማስተማር እንዲኖር መምህራን የበኩላቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የዓለም የመምህራን ቀን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) አማካኝነት በየዓመቱ በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 5 ነው የሚከበረው፡፡ ቀኑን ማክበር የተጀመረው በ1994 (እ.አ.አ) ነው፡፡ በዕለቱም የመምህርነት ሙያ ክብርን ማስጠበቅ፣ የመምህራንን ሙያዊ አቅም ማሳደግ እና ምቹ የመማር ማስተማር ሁኔታዎችን መፍጠር ላይ ትኩረት ተደርጎ ምክክር ይደረጋል፡፡

ዘጋቢ፡- ኤልያስ ፈጠነ