“ለሠላም የምንሠራው የድህረ ግጭት አውድ ጫና ውስጥ ኾነን ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

43
ባሕር ዳር: መጋቢት 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 11ኛ መደበኛ ስብሰባ ሲጀመር የምክር ቤቱ አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አሉ ያሏቸውን የሕዝብ ጥያቄዎች አንስተዋል፡፡
ከሕዝብ ተወካዮች የምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ወራት አንጻራዊ እና የተሻለ ሠላም ታይቷል ብለዋል፡፡ ሠላም አንጻራዊ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያልተፈቱ ችግሮች፣ ያልተሻገርናቸው መሰናክሎች እና የሕዝብ ሥጋቶች መኖራቸው እሙን ነው ብለዋል፡፡
ሠላም ውስጣዊ መረጋጋትን እና የጋራ ጥረትን የሚጠይቅ ሂደት ቢኾንም ኢትዮጵያ ውስጥ ፍላጎትን በኃይል፣ በመተላለፍ እና በሴራ ለመፍታት መሞከር አሁንም ሠላማዊ ነፋስ እንዳይኖር ተግዳሮት እንደኾነ በምላሻቸው አንስተዋል፡፡ ምንም እንኳን ባለፉት ስድስት ወራት የተሻለ የሠላም ሂደት ቢኖርም የጦርነት ነጋሪትን አብዝተው የሚጎስሙ ስላሉ መረጋጋት ያለ አይመስልም ነው ያሉት፡፡
ሠላም የጦርነትን ያክል ጀግንነትን ይጠይቃል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይም አዎንታዊ ሰላም ለማስፈን ብዙ ውጣ ውረድን እና ሥራን ይጠይቃል ብለዋል፡፡ ስለሠላም ስንሰራ ያለፈውን መከራ እና ፈተና ሁሉ ረስተን ሳይኾን ለዘላቂ ሠላም ስንል ይቅር ብለን መኾኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊገነዘብ ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ለሠላም የምንሰራው የድህረ ግጭት አውድ ጫና ውስጥ ኾነን ነው” ብለዋል፡፡
በጦርነት ወቅት ኃይል ማሰባሰብ ቀላል ነው ለሠላም ስትሰራ ግን ሁሉንም ኅይሎች ማሳመንን ስለሚጠይቅ ሂደቱን ፈታኝ ያደርገዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥታቸው በየደረጃው ከሕዝብ ጋር ባደረጋቸው ውይይቶች የሠላም ፍላጎት እንዳለው ስለተገነዘበ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እየተሰራ እንደኾነ አንስተዋል፡፡ ሠላም አንጻራዊ በመኾኑ እና በአንድ ጀምበር ችግሮች ስለማይፈቱ ትዕግስት፣ ትብብርን እና በጋራ መሥራትን ይጠይቃል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!