“ሀገር ማጽናት ማለት በደም እና በአጥንት የሚረጋገጥ ነው” ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)

0
102

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 03/2014 ዓ.ም (አሚኮ) “በሕግ ማስከበር እና በኅልውና ዘመቻ የተከፈለ መስዋእትነት ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና አንድነት” በሚል መሪ ሐሳብ በሕግ ማስከበር እና በኅልውና ዘመቻው ተሳታፊ ለነበሩ ጀግኖች የዕውቅና እና የምሥጋና መርኃግብር በባሕር ዳር እየተካሄደ ነው፡፡

በዕውቅና እና ምሥጋና መርኃ ግብሩ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጨምሮ የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኅላፊዎች፣ የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መሪዎች፣ የክልል ርእሳነ መሥተዳድሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ባለሃብቶች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

በመርኃ ግብሩ መክፈቻ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) ዘመቻው አማራን እና አፋርን እንደመሸጋገሪያ ቢያደርግም የአሸባሪው እና ወራሪው የትግራይ ቡድን ፍላጎት ኢትዮጵያን መበተን ነበር ብለዋል፡፡ መራር ተጋድሎ እና መጠነ ሰፊ መስዋእትነት ቢያስከፍልም ኢትዮጵያ ዳግም ማሸነፏን አረጋግጣለች ነው ያሉት፡፡ በሕግ ማስከበር እና በኅልውና ማስከበር ዘመቻው በኹሉም ዘርፍ ለተሳተፉ ዜጎች የክልሉ መንግሥት ክብር እንዳለውም ርእሰ መሥተዳድሩ ገልጸዋል፡፡

አሸባሪው ትህነግ ካለፈ ስሕተቱ መማር እንደማይችል እና ለዳግም ወረራ ዝግጅት እያደረገ መኾኑን ርእሰ መሥተዳድሩ ጠቁመዋል፡፡ ይኽ የዕውቅና እና የምሥጋና መርኃ ግብርም ላለፈው ምሥጋና ለመጪው ደግሞ መስፈንጠሪያ ነው ብለዋል፡፡

ጦርነቱ መስዋእትነትን ቢያስከፍልም፣ ሃብትና ንብረት ቢወድምም በርካታ ሰብዓዊ አርበኞች የፈለቁበት እና የኢትዮጵያ አንድነት የተረጋገጠበት እንደነበርም ርእሰ መሥተዳድሩ ተናግረዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ ከጭና እስከ ጋይንት፣ ከጋሸና እስከ ቆቦ፣ ከደሴ እስከ ጃማ፣ ከቦሩ ሜዳ እስከ ቀወት፣ ከሽዋ ሮቢት እስከ ኮምቦልቻ በርካታ ጭፍጨፋ እና ውድመት ማድረሱን ዶክተር ይልቃል አውስተዋል፡፡ ነገር ግን ለኢትዮጵያ አንድነት ምሳሌ የኾኑ ከወርቄ እስከ ድሬ ሮቃ፣ ከጻግብጅ እስከ ኬሚሴ በርካታ የጀግንነት አካባቢዎችም ተፈጥረዋል ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ፡፡

የሃይማኖት አባቶች፣ የዘመኑ አርበኞች እና ወጣቶች ተጋድሏቸው የላቀ ነበርና የክልሉ መንግሥት ምሥጋናው ከፍተኛ እንደኾነም ተናግረዋል፡፡

“ሀገር ማጽናት ማለት በደም እና በአጥንት የሚረጋገጥ ነው” ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ፡፡

የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ክልል ልዩ ኀይል፣ የክልል የፀጥታ መዋቅር፣ ፋኖ፣ ሚሊሻ እና ሕዝባዊ ሠራዊት ለፈጸሙት ዘመን የማይሽረው ተጋድሎ የክልሉ መንግሥት ያለውን ክብርና ምሥጋና ገልጸዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች እና የፌደሬሽን ምክር ቤት፣ የፌዴራል ተቋማት፣ ክልሎች፣ ባለሃብቶች፣ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት እና ድርጅቶች ላደረጉት አስተዋጽኦ ርእሰ መሥተዳድሩ በክልሉ ሕዝብ ሥም አመስግነዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ︎‼
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ ‼

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/