ሀገራዊ ችግሮችን ለመፍታት ለሀገር በቀል የሽምግልና ሥርዓት ተገቢው እውቅና ሊሰጥ እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡

351

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 28/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ባሕላዊ የሽምግልና ሥርዓት ለሰብዓዊነት፣ ለእኩልነት፣ ለመቻቻል፣ ለመልካም አስተዳደር መስፈን እና ለፍትሕ ሥርዓት ግንባታ ትልቅ ሚና አላቸው፡፡ የሚፈጠሩ ግጭቶችን፣ አለመግባባቶችን እና ቅራኔዎችን በመፍታት ሰላም እንዲፈጠር ሲያደርጉም ቆይተዋል፡፡

በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የባሕል ጥናት መምህር ሞገስ ሚካኤል (ዶ.ር) ባሕላዊ የሽምግልና ተቋማት በኢትዮጵያ የቀደመ ታሪክ ያላቸው፣ በማኅበረሰቡ ሃይማኖታዊ እና መሰረታዊ እሴቶች ላይ የቆሙ በመኾናቸው በተገልጋዮች ዘንድ የሚታመኑ ናቸው፡፡ ግጭቶች ሲፈጠሩ በማብረድ፣ የግጭቶችን መነሻ ቀድሞ የመለየት እና የመከላከል ሚናቸው የጎላ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ ዘመናዊ የፍትሕ ሥርዓት በቀላሉ ተደራሽ ባልኾነባቸው ገጠራማው የሀገሪቱ ክፍል ሰላምን በማስፈን የማይተካ ሚና እንደነበራቸው ዶክትር ሞገስ ገልጸዋል፡፡

እንደ አውጫጭኝ፣ አፈርሳታ፣ ሌባሻይና ሼንጎ የመሳሰሉ ጥንታዊ የግልግል እና የእርቅ ሥርዓቶች ባለፉት ሥርዓቶች ተግባራዊ ከተደረጉት መካከል እንደሚገኙበት ዶክተር ሞገስ ለአብነት አንስተዋል፡፡

ሀገር በቀል ተቋማቱ በሕቡዕ ተፈጽመው በመደበኛ ፍትሕ ሥርዓቱ መፍትሔ ያላገኙ ችግሮችን ጭምር በማሕላ እና በመሳሰሉ ባሕላዊ መንገዶች በመለየት አጥፊውን የመቅጣት እና ተበዳዩን የመካስ ሚናቸው የጎላ ነው፡፡ በዚህም ከመደበኛ የፍትሕ ሥርዓቱ በተሻለ መንገድ ችግር ፈች ናቸው ይላሉ መምህሩ፡፡ በዚህም በማኅበረሰቡ ተመራጭ ያደርጋቸዋል፡፡

ልማዳዊ የፍትሕ ተቋማት በማኅበረሰቡ ለምን ተመራጭ ኾኑ?

•በቤት፣ በሃይማኖታዊ ተቋማት፣ በገበያ አካባቢዎች የበዓላትን ቀን መሰረት በማድረግ ሥርዓቱ ይካሄዳል፡፡ ይህም በመደበኛ የፍትሕ ተቋማት ፍትሕ ለማግኘት ለትራንስፖርት እና መሰል ነገሮች የሚወጣውን ወጭ ያስቀራሉ፤ የሥራ ሰዓት እና ጉልበት እንዳይባክንም ያደርጋሉ፡፡

•ልማዳዊ የፍትሕ ሥርዓት በሃይማኖት ተቋማት መከናወናቸው ደግሞ ግጭት ውስጥ በገቡ አካላት፣ በምስክሮች እና በሽማግሌዎች ላይ ከፍተኛ አዎንታዊ የሥነ ልቦና ጫና ስለሚፈጥሩ ምስክሮች ለመመስከር፣ ሽማግሌዎች ውሳኔ ለመስጠት፣ ግጭት ውስጥ የገቡት አካላት ደግሞ የተላለፈውን ውሳኔ ለመቀበል አያቅማሙም፡፡

•የሽምግልናው የመጨረሻ ግብ ማሳታረቅ በመኾኑ ግጭቱ መፍትሄ እንዲያገኝ እና ደፍርሶ የነበረው ማኅበራዊ ሕይወት እንደገና እንዲቀጥል ያደርጋሉ፡፡ ግጭት ፈጣሪዎቹ ከበቀል እና ከቂም በመላቀቅ ወደ መደበኛ ሕይወታቸው እንዲመለሱ ያደርጋል፡፡

መደበኛ የፍትሕ ሥርዓቱ ዋና ዓላማ ደግሞ ማስታረቅ ላይ የተመሰረተ ሳይኾን አጥፊውን በገንዘብ፣ በእስራት ወይንም በሞት እንዲቀጣ ማድርግ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በትውልድ መካከል ቂም በቀል የሚያነግስ እንደኾነ ነው ያነሱት፡፡ በግድያ ምክንያት በእስራት ተቀጥቶ ውሳኔውን ጨርሶ የወጣ ግለሰብ ጉዳዩ በሽምግልና ካላለቀ ችግሮች እንደገና ማገርሸታቸው እንደማይቀር አስረድተዋል፡፡

•ባሕላዊ የፍትሕ ተቋማት በሕዝቡ ውስጥ ለዘመናት በቆዩ እምነቶች እና ሥርዓቶች ላይ የተመሰረቱ በመኾናቸው የሽማግሌዎችን ውሳኔዎች ለመፈጸም ያን ያህል አስገዳጅ ኀይል አይኖረውም፡፡ በመደበኛ የፍትሕ ሥርዓት ውሳኔዎችን በፖሊስ እና በፍርድ ቤት በመሳሰሉ አስገዳጅ ኀይሎች ሥለሚፈጸም ባሕላዊውን ሥርዓት የተሻለ ተመራጭ ያደርገዋል፡፡

•ባሕላዊ የፍትሕ ሥርዓት በሕዝቡ ነባር የግብረገብ መሰረቶች ላይ መነሻ ያደረገ በመኾኑ ተዓማኒነት አለው፡፡ የሽማግሌ መረጣ፣ የድርድር ጊዜና ቦታ ከማንኛውም ጣልቃ ገብነት ውጭ በኾነ መንገድ በበዳይ እና በተበዳይ ቡድኖች በኩል ስለሚወሰን በሽማግሌዎቹ የተላለፈው ውሳኔ በኹለቱም በኩል ተቀባይነት እንዳለው ገልጸዋል፡፡

•የሽምግልና ጊዜና ቦታ በበዳይ እና በተበዳይ በኩል የሚወሰን በመኾኑ ባሕላዊ የሽግልና ሥርዓቱን ተመራጭ ያደርገዋል፡፡ ሽማግሌዎች ለድርድር እና እርቅ የተለያዩ ጥረቶችን ያደርጋሉ፡፡ የሚመረጡ የሀገር ሽማግሌዎች ‹‹ለነፍሳቸው ያደሩ ናቸው›› ተብሎ ስለሚታመን የሚወስኑትን ውሳኔ ኹለቱ ቡድኖች ያለምንም መጠራጠር ይቀበላሉ፡፡ ሽማግሌዎችን እና የሽምግልና ጊዜ እና ቦታን በመቀየር የሃይማኖት ተቋማት ጣልቃ እንዲገቡ ስለሚያደርጉ ባሕላዊ ሽምግልናው የተሻለ ተቀባይነት እንዳለው ነው ዶክተር ሞገስ የነገሩን፡፡

መደበኛ የፍትሕ ተቋማቱ በአብዛኛው በገንዘብ፣ በጉልበት እና በጊዜ በኩል አባካኝ ከመኾናቸው ባሻገር አገልግሎታቸው በሥራ ቀናት መኾኑ ተመራጭ አይደሉም ነው ያሉት። ዓላማውም አጥፊውን መለየት እና መቅጣት ላይ ያተኮረ በመኾኑ ተመራጭነታቸው ዝቅተኛ ነው ብለዋል፡፡

ዶክተር ሞገስ እንዳሉት ባሕላዊ የሽምግልና ሥርዓት በመደበኛ ፍትሕ ሥርዓቱ ላይ የሚደርሰውን ጫና በመቀነስ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው፡፡ እነዚህ የፍትሕ ተቋማት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ቢኖራቸውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት ተገቢውን ሕጋዊ እውቅና አልሰጣቸውም፤ ለሀገር ሽማግሌዎችም ተገቢውን ክብር እና ጥቅማጥቅም የማስከበር ችግሮች እንዳሉ በተደጋጋሚ የሚነሱ ጉዳዮች መኾናቸውን አንስተዋል፡፡

አኹን ላይ በሀገሪቱ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ከተፈለገ ‹‹የሀገሩን ሰርዶ በሀገሩ በሬ›› እንደሚባለው ለሀገር በቀል የሽምግልና ሥርዓት ተገቢውን እውቅና መስጠት እንደሚገባ ነው መምህሩ ያነሱት፡፡

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/