ʺድል ለእርሷ ተሰጥቷል፣አሸናፊነት ከእርሷ ጋር ተሰርቷል”

323

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 14/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ሠንደቋን ያስቀደሙት ሁሉ አሸንፈዋል፣ በኩራት ሄደው በድል ተመልሰዋል፣ በጀግንነት ተራምደው፣ በኩራት ኖረዋል፡፡ ከሠንደቋ ጋር ድል አለ፤ እርሷን ጠርቶ ያላሸነፈ፣ እርሷን ይዞ መከራውን ያላለፈ የለም፡፡
እርሷን ይዞ ወደ ጦር ሜዳ የተጓዘው ሠራዊት ድል አድርጎ ሠንደቋን ከፍ አድርጓል፣ በፊቱ ያሉትን ጠላቶች ሁሉ ጥሏል፣ የጠላቶቹን አንገት አስደፍቶ ሠንደቋን ከፍ አድርጎ ሰቅሏል፡፡ ሠንደቋ ጨለማውን እያበራች፣ ማዕበሉን እያበረደች፣በመንገዷ የቆመውን እየጣለች፣ እምቢ ያለውን እያስገበረች፣ ማን ነክቶኝ ያለውን እያንበረከከች፣ወደ ድል ብቻ ትገሰግሳለች፡፡
አረንጓዴ፣ ቢጫ ቀዩ ሠንደቅ ሲነሳ ድል አብሮ ይነሳል፡፡ በአሻገር የጠሏትን በቅርብ ሄዳ ታሸንፋቸዋለች፣ የገፋትን ትጥለዋለች፣የነካትን ትሰብረዋለች፣ የወደዳትን ታከብረዋለች፣ ከፍ ያለ ግርማ ትሰጠዋለች፡፡ እርሷ ሲወዷትም ሲጠሏትም መልስ ታውቃለችና፡፡

የኢትዮጵያ ሠንደቅ ከፍ እንጂ ዝቅ ያለበት ዘመን የለም፣ አይኖርምም፤ ኢትዮጵያውያን የሠንደቅ ክብር፣ የሀገር ፍቅር ምን እንደኾነ ጠንቅቀው ያውቃሉና፣ ሠንደቃቸውን እያስቀደሙ ድል በድል እየኾኑ ይመለሳሉ፡፡ የኢትዮጵያን ሠንደቅ አስቀድሞ የገሰገሰው የኢትዮጵያ ሠራዊት የነጭ ወራሪን ድባቅ መትቶ በዓድዋ ተራራ ላይ ሠንደቁን ከፍ አድርጎ ሰቀለ፣ የኢትዮጵያን ሠንደቅ አስቀድመው የዘመቱት ጀግኖች አርበኞች ለዳግም ወረራ የመጣውን ጠላት እንዳልነበር አድርገው በየጎራው ሠንደቁን አውለበለቡ፡፡
የኢትዮጵያን ሠንደቅ አስቀድሞ የዘመተው የኢትዮጵያ ሠራዊት የሶማሊያን ወራሪ ድምጥማጡን አጥፍቶ በረሃ በበዛበት፣ ነዲድ የኾነ ሙቀት ባየለበት በካራማራ ላይ ከፍ አድርጎ አውለበለበ፡፡ ከዓድዋ አስቀድሞ፣ ከዓድዋም ተከትሎ በተነሱ ጦርነቶች ሁሉ ኢትዮጵያውያን ሠንደቃቸውን አስቀድመው እየዘመቱ በድል ተመልሰዋል፡፡ በአሸናፊነት ገስግሰዋል፡፡ ጠላታቸውን ሁሉ አንበርክከው በግርማ ተረማምደዋል፡፡

ኮሪያ በጦርነት በነበረችበት ዘመን ከልዩ ልዩ የዓለም ሀገራት የተውጣጡ ወታደሮች ወደ ኮሪያ ዘመቱ፡፡ ከዘመቱት ወታደሮች መካከል የኢትዮጵያ ወታደሮች ይገኙበት ነበር፡፡ መጠሪያ ስማቸውም ቃኘው ነበር፡፡ ከዚያና ከዚሕ እየቃኙ ድል የሚያመጡ ጀግኖች ነበሩና፡፡ በጦርነት ሕግ መሞት፣ መግደል፣መማረክና መማረክ ይገኙበታል፡፡ ወደ ኮሪያ የዘመቱት የኢትዮጵያ ጀግኖች ግን ይማርካሉ እንጂ አይማረኩም ነበር፡፡
አንድም ጠላት የኢትዮጵያን እጅ የመያዝ እድል አላገኘም፡፡ የዘመኑትና በጀግንነታቸው የሚኩራሩት ሀገራት ወታደሮች ጦርነቱ ሲያይልባቸው እጃቸውን እየሰጡ ሕይወታቸውን ያተርፋሉ፡፡ እንዲያም ሲል የት ደረሱ ሳይባል ይጠፋሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ግን ይሄን አያውቁትም፡፡ መድፉ ሲያጓራ፣ ጥይት ሲዘራ እነርሱ ከምሽግ ምሽግ እየተረማመዱ፣ ጠላትን ይደመስሳሉ፡፡ ድል ያመጣሉ፡፡ ምሽግ ሰብረው ይማርካሉ እንጂ እጃቸውን በፍጹም አሳልፈው አይሰጡም፡፡ ጦርነቱ ሲጠናቀቅ አንድም የቃኘው ሻለቃ የኢትዮጵያ ሠራዊት እጁን አልሰጠም፡፡ አንድም አልጠፋም፡፡
ይሄን ያዩት የዓለም ሀገራት አብዝተው ተደነቁ፡፡ በዚያ ዘመን የፈጸሙት ጀብዱ ከሁሉም ላቅ ያለ ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን ባሳዩት ጀግንነት ለክብራቸው ይኾን ዘንድ ሠንደቋ ከሁሉም ከፍ ብላ፣ ስለ እርሷ እየተዘመረ ለረጅም ሰዓት ተጨበጨበላት፣ ላቅ ያለ ክብርም ተሰጣት፡፡

ይሄም ዘመን አለፈ፡፡ ሌላም ድንቅ እውነት አለ፤ ኮንጎ የቤልጅየም ቀኝ ተገዢ ኾና ለዓመታት ከቆየች በኋላ ብሔራዊ ሸንጎ አቋቋመች፡፡ በተቋቋመው ሸንጎ ምርጫ አደረገች፡፡ በምርጫውም በፓትሪስ ሉሙምባ የሚመራው የኮንጎ ብሔራዊ ንቅናቄ አሸናፊ ኾነ፡፡ የቀኝ ገዢዋ ቤልጄም መንግሥት ሹማምንት እየመረራቸውም ቢኾን ፓትሪስ ሉሙምባን የሀገሪቱ መሪ አድርገው መረጡ፡፡ ኮንጎም የመጀመሪያውን ሪፐብሊክ መንግሥት መሥርታ ነጻነቷን አወጀች፡፡ ቤልጄም ድንገት ኮንጎ ከእጇ ስታመልጣት ታወቃት፡፡ አብዝታ ተናደደች፡፡ የተበሳጨችው ቤልጄም በኮንጎ ላይ ጦርነት አወጀች፡፡
አዲሱ መንግሥት የወራሪውን ጦር መቋቋም አልቻለም ነበርና የጦር እርዳታ እንዲደረግለት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጠየቀ፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም የቤልጄም ሠራዊት ከኮንጎ እንዲወጣ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ የጸጥታው ምክር ቤትም በቤልጄዬም ላይ እርምጃ ይወሰድ ዘንድ ወሰነ፡፡ የተመድ አባል ሀገራትም ሠራዊታቸውን ወደ ኮንጎ እንዲልኩ ተጠየቀ፡፡
የአሸናፊዎች ሀገር ኢትዮጵያም በተጠየቀችው መሠረት ሠራዊቶቿን ወደ ኮንጎ ላከች፡፡ ከራስ በላይ የሚያስቡት እነዚያ ጀግና የሠራዊት አባላት በንጉሠ ነገሥቱ ትዕዛዝ አማካኝነት ሠንደቃቸውን አስቀድመው ኮንጎ ገቡ፡፡ የዚያም ሠራዊት መጠሪያ ጠቅል ይባል ነበር፡፡ ንጉሡና ኢትዮጵያውያን የሚኮሩባቸው ጀግኖቹ በኮንጎ ሰማይ ሥር አስደናቂ ጀብዱዎችን ፈጸሙ፡፡ እትብታቸው ከተቀበረበት ምድር አልፈው ሰላማችንን መልሱልን፣ ነጻነታችንን አውጁልን ብሎ ለጠራቸው ለኮንጎ ሕዝብ ደረሱ፡፡

በጦርነት ውስጥ ከመዋጋት ባለፈ ሌትናል ጄኔራል ከበደ ገብሬ፣ ኮሎኔል ወርቁ መታፈሪያና ብርጋዴር ጄኔራል አበበ ተፈሪ የተባሉ የኢትዮጵያ ጀግኖች በኮንጎ ሰማይ ሥር የሠራዊት አዛዥ ኾነውም ሠርተዋል፡፡ ሠንደቋን አስቀድመው የሚገሰግሱት ድል አድርገው ይመለሳሉ፡፡ ነጻነት ያጣውን ነጻነቱን ይሰጣሉ፣ ሰላም የተነፈገውን ሰላሙን ይመልሳሉ፡፡
ኢትዮጵያዊያን ጀግኖች ደማቸውን አፍስሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው፣ ሕይወታቸውን ገብረው ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን አኮሩ፡፡
ዘመን ዘመን እየተካ ዛሬ ላይ ደረስን፡፡ በሰላሙ ትግል ሠንደቋን አስቀድመው ወደ ዓለም ሀገራት የሚጓዙት ኢትዮጵያዊያን በድል እየገሰገሱ ነው፡፡ በሚጠሏትም በሚወዷትም ፊት ሠንደቋ በኩራት እየተውለበለበች ነው፡፡
ሠንደቋን አስቀድመው በአሜሪካ ሠማይ ሥር በጀግንነት እየሮጡ ያሉ የኢትዮጵያ ብርቅዬ ልጆች ሠንደቃቸውን ለብሰው፣ ጎዳናዎችን በአረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሠንደቅ አስውበው በድል እያሸበረቁ ነው፡፡ ድል ለእርሷ ተሰጥቷል፣ አሸናፊነት ከእርሷ ጋር ተሰርቷል፡፡ ዓለም ወዳም ይሁን ሳትወድ ከከፍታው ላይ የኢትዮጵያን ሠንደቅ እያየች ነው፡፡ የኢትዮጵያ መዝሙር ከፍ ብሎ ሲዘመር እየሰማች ነው፡፡ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሠንደቅ በጎዳናዎች ከፊት እየቀደመ እያስደነገጣቸው ነው፡፡ በኢትዮጵያዊያን ብቃትና የሀገር ፍቅር እየተደመሙ ነው፡፡

ሠንደቋን አክብሮ፣ ኢትዮጵያን አፍቅሮ መሸነፍ የለም፡፡ ኢትዮጵያን የወደደ፣ ሠንደቋን ያስቀደመ ሁሉ ድል ያደርጋል፡፡ በኩራት ዘምቶ በድል ይመለሳል፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/