ʺየጠላት ግልገል ቁሞ ሲያንቀራጭ፣ በአፉ አስገባበት እንደ አንቃር ቆራጭ “

0
230

ባሕር ዳር፡ የካቲት 02/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ክብር ተነካች፣ እናት ሀገር ተደፈረች ሲባል እንደ ነብር ተቆጥቶ፣ እንደ አንበሳ አግስቶ ፎክሮ ይነሳል፡፡ ከእርሱ በላይ አተኳኮስ፣ ከእርሱ በላይ ምሽግ አፈራረስ፣ ከእርሱ በላይ ጠላትን አሳፍሮ መመለስ ላሳር ነው፡፡ መገፋት የወለደው፣ የወገን ግፍና በደል ያስነሳው፣ መከራ ያሳመመው፤ ድረሱልኝ የምትል እናት ድምጽ የቀሰቀሰው፣ የሠንደቁ ፍቅር የጠራው፣ የእናት ሀገር ታሪክ አክባሪ፣ በዘመኑ ታሪክ ሠሪ ከጀግና ሕዝብ የወጣ ጀግና ስብስብ፡፡

ፈተና በበዛበት ዘመን በጽናት የሚቆም፣ ጠላት መጣ ሲባል አረንጓዴ ቢጫ፣ ቀዩን ሠንደቅ አስቀድሞ የሚተምም፣ እናት ሀገሩን ከምንም የሚያስቀድም፣ ለተራበ አጉራሽ፣ ለታረዘ አልባሽ፣ ጠላት ሲመጣ ተኳሽ፣ በግራ እጁ እርፉን፣ በቀኝ እጁ ምንሽሩን፣ መውዜርና በልጅጉን ጨብጦ የሚኖር፡፡ ከላሞቹ ወተት፣ ከበሬዉቹ እሸት የማያጣ፣ በክረምት በጭቃ፣ በበጋ በነዳድ ጸሐይ ደከመኝ ሳይል አገላብጦ የሚያርስ፣ አሳምሮ የሚያፍስ፣ በእርሻው መካከል ጠላት ሲመጣም ከሞፈሩ ሥር ሆኖ የሚተኩስ፣ ተመልከት ብሎ አናት የሚያፈርስ ጀግና ሕዝብ፡፡

በወገኑ ላይ ከባድ ጋር የማይመሰጥር፣ በጀግንነቱ የማይጠረጠር፣ የሀገር ዋልታና ማገር፣ ንቅንቅ የማይል አጥር፣ ኢትዮጵያን አብዝቶ የሚወድ፣ በፍትሕ የሚፈርድ፣ ጠላትን በግርማው የሚያስርድ፣ ለጥል የመጣን የሚያሰግድ፣ ሀገር እነካለሁ ያለውን የሚያሳድድ ድንቅ ሕዝብ ነው አማራ፡፡ አማራ ሀገር በምትድነበት፣ ጀግንነት በሚሰራበት፣ ሕይዎት ተገብሮ ሠንደቅ ከፍ በሚልበት፣ ለፍትሕ ለነጻነት በሚቆምበት፣ አንድነት በሚጸናበት ሁሉ ይገኛል፡፡ በአራቱም ንፍቅ ዘማች፣ በአራቱም ንፍቅ ተኳሽ፣ በአራቱም ንፍቅ ፈጥኖ ደረሻ፣ በአራቱም ንፍቅ ጠላትን መላሽ ነው፡፡ ከጀግናው ሕዝብ አብራክ የተፈጠሩ፣ በዱር በገደል የሚፈናጠሩ፣ ጠላት መትተው ሀገርና ሕዝብ የሚያስከብሩ ጀግኖች ለሀገራቸው ክብር፣ ለሕዝባቸው ፍቅር ሲሉ ውሎና አዳራቸው ምሽግ ላይ ነው፡፡

ካልደረሱባቸው አይደርሱም፣ ጥይት ያለ መላ አይተኩሱም፣ ከተኮሱ አይስቱም፣ አንጥረው ይተኩሳሉ፣ ለይተው ይበጥሳሉ ከጀግና ሕዝብ የወጡት ጀግኖች የአማራ ልዩ ኃይሎች፡፡ ጠላት ፈርቷቸዋል፣ ወገን አክብሯቸዋል፣ አፈሙዛቸው እሳት ይተፋል፣ እሳቱ ይናደፋል፣ ተናድፎ ያጠፋል፡፡ ከጀግኖች መካከል ከአንደኛው ጋር ተገናኝቻለሁ፡፡

ለኢትዮጵያ ሠንደቅ ክብር ፣ ለኢትዮጵያውያን ገደብ የለሽ ንጹሕ ፍቅር ሲል 13 ዓመታት በሀገር መከላከያ ውስጥ አገልግሏል፡፡ ለመለዮው እየታመነ፣ እናት ሀገሩን ጠላት እንዳይደፍራት፣ ወንበዴ እንዳይፈነጭባት ሲል በዱር በገደል ተንከራትቷል፡፡ ኮቸሮ እየበላ፣ አንድ ኮዳ ውኃ ለሳምንት እየጠጣ ለእናት ሀገሩ ሲል ምቾቱን ረሳ፡፡ ምቾትና ደስታዬ፣ ክብርና ማረጌ ኢትዮጵያ ናት እያለ ሁሉን ለእርሷ ሰጠ፡፡ ሠንደቁን እያስቀደመ ለእናት ሀገር ክብር ሲል ታገለ፡፡ ዳሩ አይዞህ በርታ ያለው አልነበረም፡፡ በዘመኑ የነበሩ የጦር መሪዎች እርሱን እና ጓደኞቹን ሰበብ እየፈለጉ ያንገላቷቸው ጀመር፡፡

ኢትዮጵያን ብለው በተንከራተቱ በደል በዛባቸው፡፡ ሁሉም ከኢትዮጵያ አይበልጥም ሲሉ ታግሰው ኖሩ፡፡ የበደለኞች በደል ግን እየገፋ ሄደ፡፡ የሚወደውን ሙያ ጥሎ መውጣት ግድ ኾነበት፡፡ እያመመውም ቢሆን ጥሎ ወጣ፡፡ ዋና ሳጅን ደመቀ ካሴ፡፡ ከመከላከያ ሠራዊት እንደወጣ የተመቻቸ ሕይዎት ልኑር ብሎ አላሰበም፡፡ ሀገሩን በታማኝነት ያገለግል ዘንድ የአማራ ልዩ ኃይልን ተቀላቀለ፡፡

ከጀግኖቹ አማራ ልዩ ኃይል አባላት ጋር በመሆን አያሌ ጀብዱዎችን ፈጽሟል፡፡ በደል ሲፈጽሙ የነበሩትን ጠላቶች እንዳሻው ቀጥቷቸዋል፡፡ ኃይሉን አሳይቷቸዋል፡፡ ክንዱን አሳርፎባቸዋል፡፡ የአማራ ልዩ ኃይል ብዙ ግፍ የወለደው የጀግና ስብስብ ነው ይላል ዋና ሳጅን ደመቀ፡፡ የአማራ ልዩ ኃይል ጀግኖች የትህነግ ቡድን በከፈተው ጦርነት አያሌ ጀብዱዎችን ፈጽሟል፡፡ በወረሃ ጥቅምት በ2013 ዓ.ም የተቃጣበትን ጥቃት በመመከት ጠላትን አደባዬ፡፡ አሳምሮ ቀጣለው፡፡

በእብሪት የተነሳውን ጠላት ቀጥቶ አካባቢውን ነጻ አድርጎ በጀግንነት ተቀመጠ፡፡ ወራት አለፉ፤ እነ ዋና ሳጅን ደመቀም በዋገኸምራ በኩል ለወራት ቆዩ፡፡ የሽብር ቡድኑ የተሰጠውን የእፎይታ ጊዜ ተጠቅሞ ለሌላ ጥፋት ከየጎሬው ተጠራርቶ መጣ፡፡ ጀግኖቹ ተቆጥተው ተነሱ፡፡ ግዳጅ ተሰጥቷቸው ወደ ወንዳች አቀኑ፡፡ ክረምት ገብቷል፡፡ ብርዱ አሳስሮ ይጥላል፡፡ ተራራዎች በጉም ይሸፈናሉ፡፡ የሐምሌ ሰማይ ደመና እየጎተተ ዝናብ ያወርዳል፡፡ ጀግኖቹ ደግሞ ትጥቃቸውን አጥብቀው ምሽግ ውስጥ ናቸው፡፡ ብርድ ቢመጣ ውሽንፈሩ ቢበዛም እነርሱን የሚበግር አልነበረም፡፡ በዚያ ጊዜ ዋና ሳጅን ደመቀ የሻለቃ ዘመቻ ኃላፊ ነበር፡፡ ተምዘግዛጊ ነብሮቹ ወንዳች ላይ ገዢ ቦታ ላይ ምሽግ ቆፍረዋል፡፡ ጠላት እየተግተለተለ ወደ ወንዳች ይመጣ ጀመር፡፡

ʺጠላት በአራት በአምስት አቅጣጫ መጣ፡፡ እኛ ቦታ ይዘን ስለ ነበር የሚመጣውን ሁሉ የማስቀረት ሥራ ነው የሠራነው፡፡ ሁሉም እንዲመታና እንዲቀር አደረግን፡፡ ምንም ሊቋቋመን አልቻለም፡፡ በጣም ተመታ፡፡ በሲኖ ትራክ አስከሬኑን እየጫነ ኮበለለ፡፡ ቁስለኛውን በአይሱዚ ይዞ ወጣ፡፡ በወገን ላይ የደረሰብን ጉዳት አልነበረም፡፡ “ወንዳች ላይ ሀገር ለማፍረስ፣ ቀዬ ለማርከስ የመጣውን ጠላት አረገፉት፡፡ ተኩሰው የማይስቱት ጀግኖች ልኩን አሳዩት፡፡ እነርሱ አልመው ይመታሉ እንጂ ጥይት አላረፈባቸውም ነበር፡፡

ወንዳች ላይ ኃይሉ የተመታበት፣ እንደ ቅጠል የረገፈበት ጠላት በማዕበል ይመጣ ጀመር፡፡ ተምዘግዛጊ ነበሮቹም ወደ ቀበሮ ሜዳ ቦታ እንዲቀይሩ ተደረገ፡፡ በዚያም አያሌ ጦርነት ተደረገ፡፡ በወንዳች የተፈጸመው ጀብዱ በቀበሮ ሜዳም ተደገመ፡፡ አሁንም ጠላት እንደ ቅጠል ረገፈ፡፡ ጀግኖቹ በገፍ በሚመጣው ጠላት ላይ የልባቸውን ሠሩ፡፡ ወደ ወልድያም ለሌላ ግዳጅ ተላኩ፡፡ በዚያም ግዳጃቸውን በጀግንነት ፈጽሙ፡፡ ወደ ወገል ጤናም እንዲሄዱ ተደረገ፡፡ በዚህ ጊዜ ጠላት ወደ ጋይንት እየሄደ ነበር፡፡

የአማራ ልዩ ኃይል ከፍተኛ የጦር መሪዎችና የመከላከያ ከፍተኛ የጦር አዛዞች ጀግኖቹ የአማራ ልዩ ኃይሎችን በጋሸና ገብተው ጠላትን እንዲመቱ ትዕዛዝ ሰጧቸው፡፡ ዋና ሳጅን ደመቀ ኃይል መሪ ሆኖ ገባ፡፡ ሌሎች ጀግኖች የጦር መሪዎችም ውጊያውን እያነበቡ መመሪያ ይሰጧቸው ነበር፡፡ ግዳጃቸውን ጀመሩ፡፡ በሚገርም ፍጥነትና ጀግንነት ጋሸና እና አካባቢውን ተቆጣጠሩ፡፡ ወደ ጋይንት የሄደውን ጠላት ወገቡን ቆርጠው አሰቃዩት በጋሸናና እና አካባቢው የነበረውን ጠላት አዘናግተው እስኪበቃቸው ደበደቡት፡፡ የጦር ጄኔራሎቹ የልባቸውን አግኝተዋልና በልጆቻቸው ኮሩ፡፡ በጋይንት ግንባር የነበረው ሌላኛው የወገን ጦር ጠላትን እየደበደበው ነው፡፡ ወገቡ የተቆረጠበት ጠላት ከፊትና ከኋላ እየተደበደበ መመለስ ግድ አለው፡፡ ብዙውን ጠላት አስቀሩት፡፡ የቀረውን በታተኑት፡፡

እነ ዋና ሳጅን ግዳጃቸውን ፈጽመው ወደሌላ ቦታ ሄዱ፡፡ በተለያዬን ወንዝ አቅራቢያ እያሉ ዋና ሳጅን ደመቀ በሌሊት ድንገተኛ ግዳጅ ተሰጠው፡፡ ʺበተለያዬን ወንዝ ላይ እያለን ሁለት ሻንበል ይዘህ ወደ ወረባቦ ሂድ ተባልኩ፡፡ በሌሊት ይዤ ሄድኩኝ፡፡ በወረባቦ ጠላት ገዢ ቦታዎችን ለመያዝ ኃይሉን እያሰባሰበ ነበር፡፡ ወረባቡ እንደገባን ውጊያ ተከፈተ፡፡ ከመከላከያ ጋር ሆነን ስንዋጋ ዋልን፡፡ አመሻሽ ላይ መከላከያ ወደ ሌላ ግዳጅ ሄደ፡፡ ያ ቦታ ለእኛ ብቻ ተሰጠን፡፡ ቦታው አስቸጋሪ ነበር፡፡ ሌሊቱን ሙሉ ስንዋጋ አደርን፡፡ ስንዋጋም ዋልን፡፡ ጠላትም ኃይሉን እያመጣ ይጨምራል፡፡ ከሁለት ቀን በኋላ ኮማንዶ መጣልን፡፡ አንደኛውን ግንባር ሸፈነልን፡፡ ከመከላከል ወደ ማጥቃት ተሸጋግረን ቆርጠን ገብተን ጠላትን መታነው፡፡ ወደኋላ ተመለሰ፡፡ እየተከተልን ብዙ ኪሳራ አደረስንበት” ነው ያለው፡፡

ጀግኖቹ ሳይሰለቹ ጠላትን መቱ፤ ገዢ ቦታዎች ነበሩና እነዚያን ቦታዎች አሳልፈን አንሰጥም በሚል ወኔ በጀግንነት ተዋጉ፡፡ ድልም አመጡ፡፡ በተለያዩ ግንባሮች እየተንቀሳቀሱ አያሌ ጀብዱዎችን ፈጸሙ፡፡ ወደ አምደ ወርቅም ለግዳጅ ተላኩ፡፡ በአምደ ወርቅም በዲሽቃ የጠላትን የአየር መቃዎሚያ በማቃጠል ጠላትን ደመሰሱ፡፡ ወደ ደባርቅም አቀኑ፡፡ በደባርቅም እረፍት ወሰዱ፡፡ ጠላት በወሎ ተደጋጋሚ ጥቃት ይፈጽም ስለነበር ተመልሰው ወሎ ገቡ፡፡ ኩታ በር አካባቢም ከጠላት ጋር ተናነቁ፡፡ እረፍት የለሽ ጉዞ፣ እረፍት የለሽ ውጊያ፣ ለወገን የሚከፈል መስዋእትነት፣ ለሕዝብ የቆመ ጀግንነት፡፡

ያችን ቀን ዋና ሳጅን ደመቀ ሲያስታውሳት ʺጠላት ኃይሉን አጠናክሮ ነበር የመጣው፡፡ እኛ ወደ ውስጥ ገብተን እንድናጠቃ ትዕዛዝ ተሰጥቶናል፡፡ ውጊያው ተጧጡፋል፡፡ እየተዋጋን ወደ ተራራ እየወጣን ነው፡፡ ወደ ተራራው ስንወጣ ጠላት ኃይሉን አስጠግቶ ስለ ነበር ከበባ ውስጥ ገባን፡፡ እጅ ስጡ አሉን፡፡ እጅ መስጠት አይታሰብም ነበር፡፡ የጠላት ተመልካች ሰባት ሰዎች አገኘን እነርሱን ባሉበት አስቀረናቸው፡፡ ወደ ፊት ብንመለስ ጠላት አለ፡፡ አማራጫችን ወደፊት ጠላትን ሰብሮ መውጣት ብቻ ነው፡፡ ምን አይነት ውጊያ ሊገጥመን እንደሚችል ተመካከርን፣ ተስማመን፡፡ ወደፊት ገሰገስን፤ ጠላት በደፈጣ ውጊያ ገጠመን አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት መተናው፡፡ ተተኳሽ እያለቀ ነው፡፡ እኔ መገናኛ ራዲዬ ይዣለሁ፡፡ ጠላት የመጀመሪያ ትኩረቱ እኔ ጋር ነው፡፡ የእጅ በእጅ ውጊያ ገጥመናል፡፡ እጅ ስጥ ይለኛል፡፡ እጄን በፍጹም አልሰጣትም፡፡ እኔ ከተመታሁ ጦሩ ይበተናል፡፡ አራት ዙር ከበውናል፡፡ ሰብሮ ለመውጣት ከባድ ትግል ይጠይቃል”፤ ትንቅንቁ ቀጥሏል፡፡ ጥይት ያጓራል፡፡ የባሩድ ጭስ ይጎናል፡፡ አካባቢው በጥይት ታረሰ፡፡ ጀግኖቹ ያለ ምንም ስጋት በልበ ሙሉነት ይወቁት ጀመር፡፡ አማራጫቸው ማሸነፍ ብቻ ነበር፡፤ ማሸነፍ ደግሞ የዘራቸው መገለጫቸው ነውና በጀግንነት መቱት፡፡ ʺማንም ሰው እጅ እንዳይሰጥ፡፡ መሞት ካለብን በክብር እየተዋጋን በክብር እንሞታለን፡፡ ሁላችሁም እጃችሁን እንዳትሰጡ አልኳቸው፡፡ እኔ ከሞትኩ በኋላ ትወስናላችሁ፡፡ በእርግጠኝት አሸንፈን እንወጣለን አልኳቸው፡፡ ጠላት እኔን እንደሚፈልግ ገብቶኛል፡፡ ወደ ጠላት ገሰገስኩ፡፡ 21 ጓዶች ተከተሉኝ፡፡ ሌላውን ኃይል አስወጣን፡፡ እየተዋጋን፣ እየተዋጋን ሄድን፡፡ ድካም መጣ፣ ተተኳሽም እያለቀ መጣ፡፡ ሁላችንም ሦስት ሦስት ጥይት ለየራሳችን ይዘናል፡፡ የመጨረሻ አማራጭ ቢጠፋ ራሳችን የምናጠፋበት ነው፡፡ ልጆቹ ማረፍ ስላለባቸው ወደ አንድ ቤት አስገብቼ እኔ እነርሱን መጠበቅ ጀመርኩ” ነው ያለን፡፡

ከጠላት ጋር የነበረው ግብግብ በረድ ሲል ነበር ማረፍ የፈለጉት፤ መንገድ እየሰበሩ፣ ምሽግ እየደረመሱ፣ አንደኛውን ጠላት ሲያልፉ ሌላ ጠላት እየከበባቸው ነበር የሚጓዙት፡፡ ያለ ማመንታት ወደፊት ብቻ ነው ጉዞው፡፡ ʺጠላት መኖራችን ሰምቶ ወደ አለንበት ቤት መጣ፡፡ እኔ ዛፍ ተከልዬ ተቀምጬ ነበርና አላየኝም፡፡ ቦንብ ይዤ ነበር ጠላት ሲቀርበኝ በቦንብ መታኋቸው፡፡ የሞተው ሞቶ የቀረው ወደኋላ ፈረጠጠ፡፡ አንድ ብሬን ጥሎ ሸሸ፡፡ ብሬኑን አንስቼ የሚሮጠውን እያባረርኩ መታሁት፡፡ ልጆቹን አስነስቼ ቦታ ቀየርን፡፡ አሁንም ከበባ ውስጥ ገባን፡፡ እጅ ስጡ አሉን በፍጹም አልን፡፡ እኔ በተዳጋጋሚ አወጣችኋላሁ እላቸው ነበር፡፡ እጅ ሰጡ ተብለን ታሪካችን አይበላሽ፡፡ እጅ መስጠት ለእኛ ወርደት ነው፡፡ እኛ ብቻ ሳንሆን የአማራን ሕዝብም ነው የምናዋርደው አልኳቸው፡፡ ልጆቹ ጎበዞች ስለነበሩ የምለውን ይሰሙኛል፡፡ ያነሰንን ጥይት ከጠላት እየማረክን እየሞላን፡፡ ገሰገስን፡፡ ”

ዋና ሳጅን ደመቀ የመገናኛ ሬድዮ ይዞ ነበር የሚዋጋና የሚያዋጋው፡፡ ከበባው እየበዛ ሲሄ ግን ምን አልባት ከተሰዋሁ ጠላት የመገናኛ ራዲዮኑን እንዳይጠቀምበት ሲል መላ ዘየደ፡፡ አንዳቸው ከተረፉ አውጥተው ለመንግሥትና ለሕዝብ እንዲሰጡ ቃል አስገብቶ መገናኛዋን ቀበራት፡፡ እሞታለሁ እንጂ እናንተን አስዋጣችኋለሁ እላቸዋለሁ፡፡ ጥይት እየነጠቅን እየተዋጋን ስለነበር እንደምንወጣ ልቤ እየነገረኝ ነው ደመቀ ያን ጊዜ ያስታውሳል፡፡ መገናኛዋን ጠላት ያዛት ማለት የወገንን የውጊያ እንቅስቃሴ ይሰማል፡፡ በዚያ መንገድ ወገንን በቀላሉ ማጥቃት ይችላል፡፡ ዋና ሳጅን ደመቀ ግን ማጥፋት የሚገባውን መረጃ አጥፍቶ ቀብሯት ምሽግ ሰበራውን እና ግስጋሴውን ቀጠለ፡፡

ሰዓታት አልፈው ቀናት ተተካኩ፡፡ ሥንቅ የሚያቀብላቸው፣ ጥይት የሚያቀርብላቸው አልነበረም፡፡ ትጥቅ ሲያንሳቸው ጠላትን እየገደሉ እየማረኩ፣ ጥይቱን እየወሰዱ፣ ጠመንጃውን ማውጣት ከባድ ስለነበር ጠላት እንዳይጠቀምበት ከጥቅም ውጭ እያደረጉ ገሰገሱ፡፡ እየሰበሩ ወጡ፡፡ ወደ ሐይቅ በኩልም አቀኑ፡፡ የልጆቹ ፍጥነት ይገርመኛል ይላቸዋል፡፡ በሚገርም ጀግንነት ምሽግ ሰብረው ይወጣሉ፡፡

ʺእየሰበርን ስንሄድ ጠላት ኃይሉን አሰባስቦ መከላከያን ሊቆርጥ ይተጋላል፡፡ አንድ ኮሎኔል አስር ሰው ይዞ ዲሽቃ አስጠምዶ ያስተኩሳል፡፡ በዚያ በኩል ወገን ከተቆረጠ ከበባ ውስጥ ይገባል፡፡ ጠላትም ወደ ቦሩ ሜዳ ይሄዳል፡፡ ጠላት ዲሽቃ ወደሚተኩስበት ገባን፡፡ ተኳሾቹን ገደልናቸው፡፡ ዲሺቃውን ማርከን ኮሎኔሉን እዛው ገደልነው፡፡ ዲሽቃውን መሸከም አንችልም ነበርና በቦንብ አጋይተነው ገሰገስን፡፡” አራት ቀናት ኾኗቸዋል፡፡ እየሰበሩ መገስገስ ቀጥሏል፡፡ ፍጥነት፣ ስልትና ጀግንነት ይጠይቃልና ሁሉንም የተካኑበት ጀግኖች እየሰበሩ ገሰገሱ፡፡ የሚገርም ልበ ሙሉነት፣ የሚደንቅ ጀግነነት ጀግኖቹን የሚያቆማቸው ምሽግ አልነበረም፡፡ የጠላት ጥይት መቺ አልነበረም፡፡ ተኩሳቸው አያሰጋም፡፡ እኛ ግን እናድርግ ያልነውን እናደርጋለን፡፡ ከተኮስን እንደማንስታቸው እናውቃለን ነው ያለኝ፡፡

ʺየጠላት ግልገል ቁሞ ሲያንቀራጭ፣
በአፉ አስገባበት እንደ አንቃር ቆራጭ” ጠላት ሲያንቀራጭጭ፣ እየነጠሉ በአፉ እያስገቡበት፣ በግንባሩ እየለቀቁበት ጉዟቸውን ቀጠሉ፡፡ በጠላት ሬሳ ላይ እየተረማመዱ፣ ምሽግ እየናዱ ይሄዳሉ እንጂ ዝም ብሎ ጉዞ አልነበረም፡፡ ከድል ላይ ድል እየጨመሩ፣ ምሽግ እየሰበሩ በአራተኛ ቀናቸው ከወገን ጦር ጋር ተገናኙ፡፡ ሞተዋል ተብለው የነበሩት ጀግኖች በጀግንት ድል አድርገው ሲመጡ ጓደኞቻቸው ደስታቸው ኃያል ነበር፡፡ ለሌላ ድልም ተነሱ፡፡ ዋና ሳጅን ደመቀ የቀበራት የመገናኛ ሬድዮ ዛሬ ላይ ከተቀበረችበት ወጥታ አገልግሎት እየሰጠች መሆኗንም ነግሮኛል፡፡ ጠላትን መትተነዋል፣ ሙሉ ባይሆንም አንጻራዊ ሰላም አለ፡፡ ነገር ግን ደስ የሚለኝ ጠላትን አጥፍተን ስንጨርስ ነው፡፡ አሁን ደስታዬ ሙሉ አይደለም ነው ያለኝ፡፡

ʺለኢትዮጵያ ሕዝብ መሞት ኩራት ነው፡፡ እኔ እድለኛ ነኝ፡፡ በዚህ ዘመን ተገኝቼ ሀገርን አፈርሳለሁ ካለ ከሃዲ ቡድን ጋር ጦርነት በመግጠሜ፡፡ ሁሉም ለሀገሩ በአንድነት ቆሞ ጠላትን ማጥፋት አለበት” የዋና ሳጅን ደመቀ መልእክት ነው፡፡ እኔ እስትንፋሴ እስካለች ድረስ ለሀገሬና ለሕዝቤ ዘብ እቆማለሁም ብሎኛል፡፡ ለሌላ ጀብዱም ዝግጅት ላይ ነው፡፡ ወዳጄ ሀገር የጸናችው በእንደዚህ አይነት ጀግኖች ነው፡፡ ጀግኖቹ ወደ ሚገኙበት ተቋም እየተቀላቀልክ ታሪክ ሥራ፡፡ ስምህንም ከፍ አድርገህ አስቀምጥ፡፡

በታርቆ ክንዴ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Amhara Media Corporation – YouTube
youtube.com