ʺየከበረ ታሪክ ያለበት፣ አንዲት ኢትዮጵያ የጸናችበት”

47
Made with LogoLicious Add Your Logo App

ባሕር ዳር: የካቲት 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ዙሪያ ገባው በታሪክ ተከቧል፣ በቅዱስ መንፈስ ተሞልቷል፡፡ በሠርክ የአምላክ ስም ይነሳበታል፣ ገናናነቱ ይነገርበታል፣ ምስጋና ይቀርብበታል፣ ኪዳን እየተደረሰ ቅዳሴ እየተቀደሰ ለምድር በረከት ይለመንበታል፡፡ ጉባኤ ተዘርግቶ ሊቃውንቱ ምስጢር ያመሰጥሩበታል፣ ደቀመዛሙርቱ ከአበው ግርጌ ተቀምጠው እውቀት ይገበዩበታል፡፡

ሊቃውንት እየዘመሩበት፣ ደቀመዛሙርት እየቀጸሉበት፣ መነኮሳት ዳዊት እየደገሙበት፣ መቁጠሪያቸውን እየቆጠሩ የአምላክን ስም እየጠሩበት፣ ለምድር ጸጋውን እየለመኑበት፣ ምዕምናን እጅ እየነሱበት፣ ምድርና ሰማይ በምስጋና እየተናኙበት፣ የአምላክ በረከትና ረድኤት እየረበበበት ይውላል፤ ውሎም ያድራል፡፡ ግርማ በበዛበት፣ ከማዕዛዎች ሁሉ የላቀው መልካም ማዕዛ በሚያውድበት፣ ልብን በሀሴት የሚያሰግር የካህናት ዜማ በሚሰማበት፣ ለትዕዛዝ የሚፋጠኑ ዲያቆናት በሚመላለሱበት፣ የጽሕናው ድምጽ የተጨነቀን በሚያረጋጋበት፣ ከጽሕናው የሚወጣው ጭስ ወደ ሰማይ በሚያርግበት በዚያ ሥፍራ ድንቅ ነገር ሞልቷል፡፡

ንጉሥ ከፈረሱ ወርዶ ሰግዶበታል፣ በአጸዱ ሥር ቆሞ ዳዊት ደግሞበታል፣ ኪዳን አሰደርሶበታል፣ ቅዳሴ አስቀድሶበታል፣ ከካህናት መካከል ቆሞ አምላኩን አመሰግኖበታል፣ ስጋዎ ወደሙ ተቀብሎበታል፤ ሀገሩን የሚመራበት ብልሃት፣ መከራዎችን የሚሻገርበት ጽናት አምላክ ይሰጠው ዘንድ ተማጽኖበታል፣ የንጉሥ ጭፍሮች ጦራቸውን አስቀምጠው እጅ ነስተውበታል፣ በአጸዱ ሥር ተሰባስበው አምላካቸውን አመስግነውበታል፡፡ ፈረሰኛ እና እግረኛ ጦረኞች በአጸዱ ሥር ተንበርክከው ምሕላ አድርሰውበታል፡፡

ባዕት ዘግትው የሚኖሩ መናንያን፣ ሁሉም ሰው የማያያቸው ሥውር ባሕታውያን ተመላልሰውበታል፣ በመንፈስ ቅዱስ ረድኤት፣ በአምላክ ጠባቂነት በበረከት ኖረውበታል፣ በረቀቀ ሕይወት ይኖሩበታል፤ በረቀቀ ጥበብ የአምላክን ትዕዛዝ ይጠብቁበታል፣ ያስጠብቁበታል፡፡
በዚያ ሥፍራ የምድር ነገሥታትና መሣፍንት ድንኳን ጥለውበታል፣ ችሎት ዘርግተው ፍርድ ሰጥተውበታል፣ የሰማይና የምድሩ ንጉሥ ቤተ መቅደሱ ታንፆበታል፣ ስሙ እየተመሰገነ ስጋና ደሙ ተፈትቶበታል፣ መንፈስ ቅዱስ ሞልቶበታል፣ በረከትና ረድኤት ረብቦበታል፡፡ በዚያ አጸድ ሥር ተነግሮ የማያልቅ፣ ታስሶ የማይዘለቅ ታሪክ ሞልቷል፡፡

እድል ቀንቶኝ ወደ ጥንታዊቷ ከተማ ደብረ ታቦር ሄጄ ነበር፡፡ ታሪክ ያደላት፣ ሃይማኖት የጠበቃት፣ ኢትዮጵያዊነት በብርቱ ክንድ የጸናባት፣ ሠንደቅ የከበረባት ደብረ ታቦር አያሌ ታሪኮችን አቅፋለች፡፡ በየኮረብታዎቿ አብያተ ክርስቲያናት ይታያሉ፣ በየአብያተ ክርስቲያናቷ ሊቃውንትና ደቀማዝሙርት ነጭ እርግብ መስለው ይውላሉ፣ በየጎዳናዎቿ ታሪኮች ይነገራሉ፣ በየአቅጣጫው ጀግኖቿ ይመላለሳሉ፡፡

በዚሕች ከተማ በሚገኝ የከበረ ታሪክ ወደአለበት፣ የንጉሥ ቴዎድሮስ አሻራ ወደተቀመጠበት ታላቅ ቤተመቅደስ ዘንድ አቅንቻለሁ፡፡ ያ ታሪክ እንደ ብራና ተገልጦ የሚነበብበትን፣ ፈረሰኛና እግረኛ የሚታወስበትን፣ የታቦት ማደሪያ ድንኳን የሚተከልበትን የአጅባር ሜዳን በአሻገር እየቃኘሁ፣ በኮረብታዎች ላይ የተሠሩ ድንቅ አብያተክርስቲያናትን እየተመለከትኩ ወደ ከበረው ሥፍራ ተጓዝኩ፡፡ መዳረሻዬ ከፍ ባለ ሥፍራ ላይ በግርማ ይታያል፤ በአሻገር ሲያዩት ገና ኑ ቅረቡ ይላል፤ በሩቁ ይጣራል፡፡ ታላቁ ደብረ ታቦር መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን፡፡ ብዙዎች ደብረ ልዑላን እያሉ ይጠሩታል፡፡ የልዑላን መናገሻ፣ የልዑላን መዳረሻ ነውና፡፡
እስካዬው ቸኩያለሁ፤ በአጸዱ ሥር እስገኝ ድረስ ጓጉቻለሁ፣ የከበረ ታሪኩን እሰማ ዘንድ በብርቱው ወድጄያለሁ፡፡ ዙሪያ ገባውን እየቃኘሁ፣ ታላቁን ደብር በአሻገር እያየሁ ወደ አጸዱ ሥር ቀረብኩ፡፡ በዙሪያ ገባው የቆሙ ዛፎች፣ በአጸዱ ሥር ያሉ መቆሚያ መቀመጫዎች፣ ወደ ከፍታው የሚያወጡ የሚያወርዱ ደረጃዎች ሁሉ ታሪክ ያከበራቸው፣ እልፍ ታሪክ የተሠራባቸው፣ ታሪክም የሚነገርባቸው፣ መንፈስ ቅዱስ የመላባቸው ናቸው፡፡ በዚያ የከበረ ሥፍራ ደርሻለሁ፡፡ ዙሪያ ገባውንም አይቻለሁ፡፡ ንጉሥ ቴዎድሮስ ችሎት ካቆመበት ሥፍራ ቆሜ ከታሪክ አዋቂዎች ታሪክን ተቀብያለሁ፡፡
የደብረ ታቦር መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን አገልጋይ ዲያቆን ይበልጣል አድማሴ በሥፍራው ቤተክርስቲያን ከመታነፁ አስቀድሞ ቤተ መንግሥት ኾኖ ያገለግል እንደነበር ነግረውኛል፡፡ በዚያ ሥፍራ ታላቁ ራስ አሊ የመቀመጫ ቤተ መንግሥት አድርገውት ይኖሩ ነበር፡፡ ሥፍራው ያማረ ነበርና ከቦታ ቦታ አማርጠው ነበር የተቀመጡበት፡፡ ራስ አሊ በቤተመንግሥታቸው እጅግ ያማረች የእንግዳ መቀበያ ቤት ነበረቻቸው፤ ወደዚች ቤት የገቡ ሁሉ በቤቷ ውበት እየተደነቁ ጣሪያና ግድግዳዋን ያዩ ነበር፡፡ የጣሪያዋ ውቤት እጅግ ያምር ስለነበር ሁሉም አንገቱን እያቃና ያያታል፡፡ በዚህም ጊዜ ʺየአንገት እዳ” ሲሉ ስም አውጡላት፡፡ ይሔን ስም ለምን ሰጧት ቢሉ የሚመጣው ባለጉዳይ ሁሉ ውበቷን ለማድነቅ አንገታቸውን ስለሚያቃኑና ለረጅም ሰዓት ውበቷን እያደነቁ ስለሚቆዩ በዚህ ምክንያት አንገታቸው ስለሚታመም ነው፡፡
በዚያ ዘመን መሳፍንቱ በየክፍለ ሀገሩ ግዛት ይዘው ጎራ ለይተው ይኖሩ ነበር፡፡ ሀገሪቱን አንድ የሚያደርገው፣ ሁሉንም የሚያሰባስበው ዘውድ ደግሞ አቅሙ ተዳክሞ ነበር፡፡ ይህን የደከመ ዘውድ ወደ አስፈሪነቱ ይመልስ ዘንድ ራዕይ የሰነቀ በመንፈስም፣ በአካልም ጀግና የሆነ ሰው ከወደቋራ ተነስቶ ነበር፡፡ ያ ቋረኛ ጠላት በፊቱ የማይበረክትለት፣ እኔነኝ ያለ በእፍኙ የማይሞላለት፣ ግርማውን ችሎ የማይቆምለት አስፈሪ ነበር፡፡ አንደኛው መስፍን ሌላኛውን መስፍን ድል መትቶ የበላይ ለመሆን በሚጣጣርበት በዚያ ወቅት ያ ልበ ሙሉ ጀግና መስፍንነትን ሳይሆን ንጉሠ ነገሥትነትን፣ መከፋፈልን ሳይሆን አንድነትን ዓልሞ ተነሳ፡፡ ሕልሙን እውን ያደርግ ዘንድ ጉዞ ጀመረ፡፡

አካሄዱ አስፈሪ ነበርና በጦርነት የማይቻል ኾነ፡፡ በወቅቱ ከፍ ያለ ስም ያላቸው የእቴጌ መነን ልጅ ራስ አሊ ቋረኛው ካሳን በጋብቻ ይዛመዱት ዘንድ ወደዱ፡፡ እቴጌ መነን እና ራስ አሊ ተዋበችን የመሠለች ልዕልት ሰጡት፡፡ ዳሩ የራስ አሊ ስጋት አልቆዬም፡፡ ለካሳ የሰጡት ልጃቸው ተዋበች የካሳ ራዕይ የገባት፣ በርታ የምትለው ነበረች እንጂ በጋብቻ ተታልሎ ከሕልሙ እንዲቀር የምትፈልግ አልነበረችም፡፡ ራስ አሊ አማቻቸውን የሚገባውን ክብር አልሰጡትም፡፡ ለካሳ የተነፈገው ክብር ካሳን ብቻ ሳይሆን ተዋበችን አስቆጣ፡፡ ግርማዋን ታጠቅ እንድትለው፣ እርሱም የማይላላውን፣ የማይፈተውን ወኔ እንዲታጠቅ አደረገው፡፡ ይህም ታሪክ የሚመነጨው ከዚህ ሥፍራ ነበር፡፡
የቀደምት ነገስታትና መኳንንት ልማድ ነውና ከእለታት በአንድ ቀን ራስ አሊ ለአደን ይወጣሉ፡፡ በዚያም ሥፍራ አንድ ድኩላ ይመለከታሉ፡፡ ያን ድኩላም አልመው መቱት፡፡ ኢላማ ውስጥ ገብቶ የተመታውን ድኩላ ያመጡላቸው ዘንድ አሽከሮቻቸውን ላኩ፡፡

አሽከሮቻቸውም ሄደው ባዩ ጊዜ የተመታው ድኩላ ሳይሆን ፂማቸው የረዘመ፣ ጤዛ ልሰው፣ ድንጋይ ተንተርሰው፣ ድምጸ አራዊቱን ታግሰው የሚኖሩ ባሕታዊ ነበሩ፡፡ ይሄንም ያዩ አሽከሮች በድንጋጤ ለራስ አሊ ሄደው ነገሯቸው፡፡ ራስ አሊም ወደ ባሕታዊው ሄደው አዘኑ፡፡ ተፀፀቱ፡፡

በዚያም ጊዜ ባሕታዊው አይዞት አይዘኑ፡፡ የእኔ የምድር ቆይታዬ ተጠናቋል፡፡ ቦታው ትንቢት ስላለው የሆነ ነው፡፡ ከዚህ ቦታ ላይ ቅዳሴ ይቀደስበታል፣ ስብሐተ እግዚአብሔር ይደረስበታል፤ ስጋ ወደሙ ይፈተትበታል፡፡ እኔም የመጣሁት ይሄን ትንቢት ልናገር ነው፡፡ እኔም አርፋለሁ፡፡ እኔ ከማርፍበት ሥፍራም ቤተክርስቲያን ይተከላል አሉ፡፡ ባሕታዊው ይሄን በሚናገሩበት ጊዜ ልጅ ካሳ ከአማቱ ጋር ኾኖ ይሰማ ነበር፡፡ በልቡም ጠበቀው፡፡ ጊዜው እስኪደርስ ድረስ ታገሰ፡፡ ጊዜው ደረሰ፡፡

ኢትዮጵያ አንድ የምትሆንበት መሳፍንቱ ድል ተነስተው አንድ ዙፋን የሚጸናበት ዘመን ቀረበ፡፡ ልጅ ካሳ የሚያምናቸውን ሰዎች አማከራቸው፡፡ታማኙ ገብርዬ እስከ መቃብር ድረስ እንደሚታመነው ቃል ሰጠው፡፡ ተዋቡም ባሏን አጠንክራ ሂድ ታጠቅ ኢትዮጵያን አንድ አድርገህ ና አለችው፡፡ ያን ጊዜ ካሳ ወደኋላ ላይመለስ ተነሳ፡፡

አባ ታጠቅ ካሳ አጥብቆ ታጠቀ፡፡ አማቱን ጨምሮ ሌሎች መስፍኖችን ድል መታ፡፡ ንጉሠ ነገሥትም ኾነ፡፡ መናገሻውንም አስቀድመው አማቱ በነበሩበት በደብረ ታቦር አደረገ፡፡ በአንድ ወቅት ንጉሠ ነገሥት ቴዎድሮስ በዚያ ሥፍራ ችሎት ሲያደርግ አምላክ በሰው አምሳል መጣበት ይላሉ ዲያቆን ይበልጣል፡፡ ንጉሡም ይሄን ባዬ ጊዜ ለምን ወደ እኔ መጣህ? አንተ እኮ የምድርና የሰማይ ፈራጅ ነህ ? አለው፡፡ እርሱም የምፈርድበትንማ አንተ ተቀመጥክበት አለው ይላሉ፡፡ ንጉሡም ይሄን በሰማ ጊዜ ከኮረብታው ጫፍ ወርዶ ችሎቱን ወደታች አደረገ፡፡ በኮረብታው ጫፍም ቤተመቅደስ አሠራ፡፡ ቤተ መቅደሱ በተሠራም ጊዜ ቴዎድሮስ መቶ ሠሪ ሺህ አነዋሪ ቀጥሮ ነበር ይባላል፡፡ መቶው ይሠራል፣ ሺህ ሰው ደግሞ ይሄን አስተካክሉ፣ ይሄን አድርጉ እያሉ ያመላክቱ ነበር ሲሉ ነው፡፡ በቤተ መቅደሱም ታቦተ መድኃኔዓለምን አስገባ፡፡ ቴዎድሮስ ለመድኃኔዓለም ልዩ ፍቅር ያለው ንጉሥ ነበር ይባላል፡፡ ወደ ጦርነት ከመግባቱ አስቀድሞ በመድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ያስቀድሳል፤ ጸሎት ያደርሳል፡፡ ቴዎድሮስ ሥፍራውን ለሰማዩ ንጉሥ ለቅቆ ቤተ መንግሥቱን ለብቻ አደረገ፡፡

ቴዎድሮስ ደብሩን ካስደበረ በኋላ ጽናጽን ወቂ፣ አቴና ጠቅጣቂ፣ ወገብ ሰባቂ የሚባለውን ስርዓትም አስጀምሮበታል፡፡ ለጽናጽን ወቂ ሠባ፣ ለአቴና ጠቅጣቂ ሠባ፣ ለወገብ ሰባቂ ሠባ ሊቃውንት ከፈለ፡፡ እኩል አድርጎ ስርዓት ሠራ፡፡ የማሕሌት አገልጋይ ብቻ ከሁለት መቶ በላይ ነበሩት፡፡ ይሄም እርዱ የሠራው ትውፊትና ስርዓት ዛሬም በደብረ ታቦር መድኃኔዓለም ይከዋናል፡፡ ለታላቁ ደብር አሥራ አራት ገባሪ አብያተክርስቲያናት አበጀለት፡፡

በዚሕም ቤተ መቅደስ ቴዎድሮስ እየገባ ያስቀድስበት፣ ስብሐተ እግዚአብሔር ያደርስበት ነበር፡፡ ያ ሥፍራ ለኢትዮጵያ ማዕከል ኾኖ ለሀገር አንድነት የሚበጁ ሕግና ስርዓትም የረቀቀበት ነው፡፡ በቤተ ክህነቱ ሁለት ቀሳውስት፣ ሦስት ዲያቆናት ይቀድሱ የሚለው የቴዎድሮስ ትዕዛዝ ያለፈበት፣ ሥርዓትም የጸናበት በዚሑ ደብረታቦር መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን እንደኾነ ዲያቆን ይበልጣል ነግረውኛል፡፡ በቤተ መንግሥቱም ደሞዝ የሚከፈለው ወታደር እንዲኖር ቴዎድሮስ ስርዓት ያሠረበት በዚሁ ሥፍራ ነው፡፡
በዚያ ሥፍራ ከሆላንድ የመጣ ስማ ጎንደር የተሰኘ ደወል አለ፡፡ ያን ደወል እያስደወለ አንዲት ኢትዮጵያ፣ አንድ መንግሥት እያለ አዋጅ አስነግሮበታል፡፡ በሀገሬ ላይ ክንድህን የምታነሳ ሁሉ እረፍ አደብ ግዛ ብሎበታል፡፡ ደብረታቦር መድኃኔዓለም የበዙ የቤተመንግሥት እና የቤተ ክህነት አዋጆች የታወጁበት፣ ዛሬም ድረስ የፀኑ ስርዓቶች የጸኑበት ነው፡፡ ስማ ጎንደር የተሰኘው ደወል ዛሬም የቴዎድሮስን ታሪክ እየነገረና እየዘከረ በአጸዱ ሥር በክብር አለ፡፡

ደብረ ታቦር መድኃኔዓለም እቴጌ ተዋበች ያደገችበትና ለቁምነገር የበቃችበት፣ ልዑልዓለማየሁ ክርስትና የተነሳበት ታሪክና ሃይማኖት ከፍ ብለው የሚኖሩበት ነው፡፡ ቴዎድሮስ በቤተመንግሥቱ ላይ ቤተመቅደስ ሠርቶ ችሎቱን ወደታች ባወረደ ጊዜ አራት መንገዶች ወይም በሮች ነበሩ፡፡ አራቱም መንገዶች ወይም በሮች መዳረሻቸው ቤተክርስቲያኑ ነው፡፡ ወደ ችሎት የሚሄዱ ሰዎችም መጀመሪያ ወደ ቤተክርስቲያኑ ያቀናሉ፡፡ ከዚያም ወደ ችሎቱ ይመለሳሉ፡፡ ቴዎድሮስ ወደ እኔ ችሎት ከመምጣታቸው በፊት ከአምላካቸው ጋር ታርቀው መምጣት አለባቸው ብሎ ያምናል፡፡ እነዚያ በሮችም ንጉሥ በር፣ ሥዊት በር፣ ዲፕሎማት በር፣ አቤቱታ በር ይባላሉ፡፡

በታላቁ ደብር አጸድ ሥር ቴዎድሮስ የእጅ አሻራ እንዳረፈባት የሚነገርላት የደወል ቤት ትገኛለች፡፡ በእንቁላል እና በኖራ የተሠራችው ቤት ከላይ ስማ ጎንደር ደወል ይመቀጥባታል፣ ከሥር አበው ጸሎት እያደረሱ ይኖሩባታል፡፡ የነገሥታቱ ስጦታዎች፣ የረቀቁ ንዋዬ ቅድሳት በዚያ ደብር ይገኛሉ፡፡ ታሪክን፣ ሃይማኖትን፣ እሴትን፣ ኢትዮጵያዊነትን የሚገልጡ እና የሚያስተምሩ የረቀቁ ቅርሶችም አሉበት፡፡ የደብረታቦር መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን አደጋዎች ደርሰውበት አሁን ላይ ያለው ሕንጻ ቤተክርስቲያን የተሠራው በአጼ ኃይለ ሥላሴ እንደኾነ ዲያቆን ይበልጣል ነግረውኛል፡፡

ሕንጻ ቤተክርስቲያኑ በአማረ ጥበብ የተሠራ ነው፡፡ የደብረ ታቦር መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ከአስመራ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ጋር ይመሳሰላል ይባላል፡፡ አፄ ኃይለ ሥላሴ የአስመራ መድኃኔዓለምን ሕንጻ ቤተክርስቲያን ይወዱት ስለነበር የደብረ ታቦር መድኃኔዓለምም በዚያ ቅርጽ እንዲሠራ አደረጉ ነው ያሉኝ፡፡ በእሳቸው ዘመን የተመረጠለት ቀለምም ዛሬም ድረስ እንደተጠበቀ ቀጥሏል፡፡ ለምን ደብረ ታቦር መድኃኔዓለም ስርዓት የሚጸናበት፣ ትዕዛዝ የሚከበረበት የቃል ኪዳን ሥፍራ ነውና፡፡

በደብረታቦር መድኃኔዓለም አጸድ ሥር የመጽሐፍ፣ የቅኔ፣ የአቋቋም፣ የቅዳሴ፣ የድጓ፣ የዝማሬ መምህራን ጉባኤ ዘርግተው ያስተምሩበታል፡፡ ደቀመዛሙርትም በአበው እግር ሥር ተቀምጠው ይማሩበታል፡፡ በከበሩ ጉባኤያት የበዙ ሊቃውንት እና ደቀመዛሙርት መኖራቸው የታላቅነቱ መገለጫ ነው፡፡ የደብሩ አለቃ መልአከ ልዑላን፤ የአራቱ ጉባኤያት መምህር መምህረ መምህራን የሚባል ማዕረግ ይሠጣቸዋል፡፡

በታላቁ ደብር በታላላቅ በዓላት በሁለት መንበር ይቀደስበታል፡፡ የደብሩ ታላቅነት ማሳያ አንዱ ምሳሌ መሆኑም ይነገራል፤ ይሄም የጸናው እና የከበረው ስርዓት ዛሬም ድረስ ቀጥሏል፡፡ ሊቃውንት በደብረታቦር መድኃኔዓለም የሚከወነውን ማሕሌት ለማዬትና ለማስማት ከሩቅ መንገድ ይመጣሉ፡፡ ሙሽሮች የተቀደሰውን የጋብቻ ስርዓታቸውን በተክሊል እና በስርዓተ ቁርባን ለመፈፀም ይጓዙበታል፤ ስርዓቱንም ይፈጽሙበታል፤ ምዕመናን ለጸሎትና ለሱባኤ ቀን ከሌት ይጓዙበታል፤ ቦታው ስለት ሰሚ ነውና፡፡

ከቴዎድሮስ የችሎት ሥፍራ ኾኔ ታሪክን ከሚነግሩት ሥር እልፍ ታሪክ ሰማሁ፡፡ ታዲያ ምን አቅም አለኝና ያን ሁሉ ታሪክ መጻፍ ይቻለኛል? ምንስ ብርታት አለኝና ያን የመሠለ ሥፍራ በብዕሬ እገልጸዋለሁ? ከሰማሁት ጥቂቱን ተናግሬ የበዛውን ዝም እላለሁ እንጂ፡፡ ምን አይነት መመረጥ ነው? ምን አይነት መከበር ነው? ምን አይነትስ ቅድስና፣ ምን አይነትስ ልዕልና ነው? አጀብ ያሰኛል፡፡

ወደ ምዕራብ ቤቷ ለመግባት አዝግማ የነበረችው ጀንበር ስልጣኗን አሳልፋ ሰጥታ ተጠቅልላ ጠፍታለች፤ በአጸዱ ዙሪያ ገብ ያሉ ዛፎች በነፋስ እየተገፉ ያረግዳሉ፣ በዛፎቹ ሥር የቆሙ ምዕምናን ጸሎት ያደርሳሉ፡፡ በአጸዱ ሥር የሚቀጽሉ ደቀማዛሙርት በሚያምር ለዛቸው ያዜማሉ፡፡ በአጸዱ ሥር ወደ አፍንጫ የሚመጣው ማዕዛ ልብን በሀሴት ያንሳፍፋል፣ ግርማ የመላበት ደብር እጹብ ያሰኛል፡፡ ታሪክ ከነገሩኝ ጋር ኾኔ በቀስታ ቃኘሁት ግሩም ነው፡፡
ጨለማ በምድር ካበውን ሲደርብ፣ ሰውም ወደ ማደሪያው ሲያዘግም ከታሪክ ነጋሪዎቼ ጋር ወደታች ወረድኩ፡፡ እግሬ ይጓዛል፣ ልቤ ግን በመድኃኔዓለም አጸድ ሥር ያየውን ያንሰላስላል፡፡ በዚያውም ቀርቷል፡፡

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!