ʺየኢትዮጵያን ነገር ታሪክ ስትቀምሩ፣ የእምዬን መነሻ አንኮበርን ጥሩ”

0
84

ባሕር ዳር: ሕዳር 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አንዳንድ ሥፍራዎች አሉ ነገሥታቱ የሚመርጧቸው፣ አንዳንድ ቦታዎች አሉ ቤተ መንግሥት የሚታነጽባቸው፣ አንዳንድ አካባቢዎች አሉ ታሪክ ከፍ አድርጎ የመዘገባቸው፣ ትውልድ ሁሉ የሚጠራቸው፣ በልቡ ላይ ጽፎ የሚያኖራቸው፣ አንዳንድ ሥፍራዎች አሉ ሕዝብ የሚሰበሰብባቸው፣ አንዳንድ ሥፍራዎች አሉ የአንድነት ውል የሚታሰርባቸው፣ የሀገር ስም ከፍ ብሎ የሚጠራባቸው፣ሠንደቅ ከከፍታው ላይ የሚውለበለብባቸው፣ ዙፋን የሚቀመጥባቸው፣ ነገሥታቱ በኩራት የሚኖሩባቸው፣ መኳንንቱና መሳፍንቱ በክብር የሚመላለሱባቸው፣ የጦር አበጋዞች፣ የእልፍኝ አስከልካዮች በኩራት የሚታዩባቸው፡፡
ይህች በታሪክ የከበረች፣ ለስመ ገናነት የተመረጠች፣ ሠንደቅ በኩራት እንዲውለበለብባት የታደለች፣ ነገሥታቱን ያስቀመጠች፣ መኳንንቱን እና መሳፍንቱን መኩራት ያመላለሰች፣ የጦር አበጋዞችን በጀግንነት ያኖረች ውብ ሥፍራ ናት፡፡

ስሟ ከፍ ከፍ ብሎ ይጠራል፣ ታሪክ ስለ እርሷ ይመሰክራል፣ ዘመን እርሷን ይዘክራል፡፡ ትውልድ በታሪኳ ይኮራል፡፡ የሸዋ ነገሥታት በክብርና በፍቅር ኖሩባት፣ በብልሃት አስተዳደሩባት፣ በጀግንነት እና በኩራት ተመላለሱባት፣ ዙፋን አጸኑባት፣ ታሪክ ሠሩባት፡፡ የሸዋ መኳንንት ስለ ሀገር አንድነት፣ ስለ ጸና ኢትዮጵያዊነት፣ ጠላት ስለማይደፍረው ጀግንነት፣ ዘመን ስለማይሽረው ሀገር ወዳድነት መከሩባት፡፡ ምክራቸውንም አጸኑባት፡፡

የአቤቶ ስብስቴ (ሰባስትያኖስ) ልጅ መርድ አዝማች አብዬ የክርስትና ስማቸው ቀዳሚ ቃል ከአባታቸው አልጋ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ በዘመኑ ሠራዊት የሚሰፍርባቸው፣ ድንኳን የሚጣልባቸው ከተማ ይሆኑ ነበር፡፡ አያሌ ነገሥታት በተጓዙበት፣ ድንኳን ጥለው ባረፉበት ሥፍራ ሁሉ ከተማ ይቆረቁሩ፣ ስልጣኔን ያስጀምሩ ነበር፡፡ መርድ አዝማች አብዬም የሐር አምባን ከተማ ቆረቆሩ፡፡ በቆረቆሯት ከተማም የቅዲስ ሚካኤልን ደብር ደበሩ፡፡ መርድ አዝማች አብዬ በዘመናቸው የወታደርነት፣ የግብርና ሥራና የቤተ መንግሥት ሥራን አስፋፉ፡፡ መርድ አዝማች አብዬ የሐር አምባን ቆርቁረው አላረፉም፡፡ ከሐር አምባ ተነሰተው ወደ ሌላ ሥፍራ አቀኑ፡፡ የአንኮበር ከተማንም ቆረቆሩ፡፡ መርድ አዝማች አብዬም በፍቅርና በደስታ አገልግለው ዘመናቸው ተፈጸመ፡፡

የመርድ አዝማች አብዬ ልጅ መርድ አዝማች አምኃየስ በአባታቸው አልጋ ተቀመጡ፡፡ መርድ አዝማች አምኃየስ አባታቸው የቆረቆሯትን ከተማ የበለጠ አስዋቧት፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስን ቤተክርስቲያንን ሠርተው ከተማዋን ሌላ ውበት ጨመሩላት፡፡
መርድ አዝማች አምኃየስም አለፉ፤ ልጃቸው መርድ አዝማች አስፋወሰን አልጋውን ተረከቡት፡፡ የአንኮበርንም ከተማ ከቀደመው የተሻለ አስዋቡ፡፡ መርድ አዝማች አስፋወሰን እንደ አባታቸው ሁሉ ደብር መደበር ፈለጉ፡፡ የቅድስት ማርያምን ቤተከርስቲያንም አሰሩ፡፡ ይህም አንኮበር የበለጠ እያማረች፣ ከፍ ከፍም እያለች እንድትሄድ አደረጋት፡፡ ለመኳንንቱና ለመሳፍንቱ፣ ለሊቃውንቱ መቀመጫነት ተመረጠች፡፡ ፍትሕ ሊጠይቅ፣ በቤተመንግሥት ከሚገባው ግብር ለመቋደስ የሚመጣው ሕዝብም እየበዛ ሄደ፡፡

ተክለጻዲቅ መኩሪያ ከአፄ ልብነ ድንግል እስከ አጼ ቴዎድሮስ በሚለው የታሪክ መጽሐፋቸው እንዳሰፈሩት ከመርድ አዝማች አብዬ የጀመረው የስልጣን ተዋረድ በአንኮበር ከፍ ብሎ ቆይቷል፡፡ ከተማዋንም የቆረቆሯት መርድ አዝማች አብዬ መሆናቸውን ጽፈዋል፡፡ አንኮበር ረዘም ላለ ጊዜ ለሸዋ ነገሥታት መቀመጫ ኾና ብትቆይም ስሟ የናኘው ግን በዘመነ ምኒልክ ነበር፡፡ ብዙዎችም አንኮበር ስትነሳ ምኒልክን አብረው ያነሳሉ፣ ምኒልክም ሲነሱ አንኮበርን ያስታውሳሉ፡፡ አንኮበር ግን ከዘመነ ምኒልክ አስቀድማ የተመሠረተች፣ አያሌ የሸዋ ገዢዎችን ያየች፣ በታሪክ የደባረች ከተማ ናት፡፡

የአንኮበር ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሪት ዓለምሸት ላቀው ደግሞ አንኮበር በ333 ዓ.ም በአብረሃ ወአፅብሀ ዘመነ መንግሥት እንደተቆረቆረች ይነገራል ብላኛለች፡፡ ይህም ዘመን ተክለጻዲቅ እንደ ቆረቀሯት ከሚያነሱት ከመርድ አዝማች አብዬ በርካታ ዓመታትን ወደ ኋላ የሚያስቆጥር ነው፡፡ ይህች የታሪክ አምድ የሆነች ውብ ሥፍራ አያሌ ታሪኮች ተሰርተውባታል፡፡ አንኮበር ምኒልክ የሸዋ ንጉሥ በነበሩበት ዘመን ረዘም ላሉ ዓመታት የተቀመጡባት፣ ከእርሳቸው አስቀድመው የነበሩት የሸዋ ነገሥታትም ዙፋናቸውን ያረጉባት ከተማ ናት፡፡ ኃያሉ ንጉሥ ምኒልክ ዙፋናቸውን ወደ እንጦጦ እስካዞሩበት እና እቴጌ አዲስ አበባን እስካቋቋሙበት ዘመን ድረስም ይህችው ታሪካዊት ሥፍራ የዙፋን መቀመጫ፣ የመኳንንቱና የመሳፍንንቱ መውጫ ነበረች፡፡
በንጉሥ ሳሕለ ሥላሴ ዘመን ጊዜ ያመረ ቤተ መንግሥት ተሰርቶባት ነበር፣ ምኒልክ በነገሡም ጊዜ የበለጠ አስበውት እንደኖሩ ይነገራል፡፡ በከፍታ ላይ የተሰራ፣ ከፍ ያለ ታሪክ የተሠራባት፣ አያሌ ነገሥታት የተመላለሱበት፣ አስፈሪ የጦር አበጋዞች የታዩበት፣ ቤተ መንግሥቱን ዙሪያ ገብ የጠበቁት፣ በአንድነት መክረው ሀገር ያጸኑበት ሥፍራ በዙሪያ ገባው የሚያስቃኝ ድንቅ ቦታ ነው፡፡ ለወትሮው ነገሥታት ከፍ ያለ ቦታ ምርጫቸውና አንኮበርንም የመረጡበት ከፍ ብላ ስለተገኘች፣ ለቤተ መንግሥት የተገባች ስለነበረች ነው፡፡

የአንኮበር ቤተ መንግሥት ተፈጥሮ ባስዋባትና በሞሸራት ምድር የተገነባ ነው፡፡ ከቤተ መንግሥቱ ሰገነት ላይ ኾኖ የአፋር ዝቅተኛ ስፍራዎችን እስከ አዋሽ ድረስ መመልከት እንደሚያስችል ወይዘሪት ዓለምሸት ነግራኛለች፡፡ በ2 ሺህ 870 ሜትር ከፍታ ላይ እንደሚገኝ የሚነገርለት ይሄ ባለ ግርማ ሞገስ ቤተ መንግሥት የከበሩ ታሪኮችን እየመሰከረ ዘመናትን ተሻግሯል፡፡ ኢጣሊያ ዓድዋ ላይ እንዳልነበር ያደረጓትን እምዬ ምኒልክን ትበቀል ዘንድ ስለ ወደደች በዘመነ ኃይለ ሥላሴ ባደረገችው ወረራ ቤተ መንግሥቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሳበታለች፡፡ ዳሩ የዓድዋን ታሪክ ማጥፋት፣ የአንኮበርንም ዝና ማጥፋት አልቻለችም፡፡
በዚህ ሥፍራ ታሪክን የሚዘክር በመድኃኔዓለም ቤተ ክርስትያን አጸድ ሥር ሙዝየም አለ፡፡ በሙዝየሙ ውስጥ ነገሥታቱ ይገለገሉባቸው የነበሩ ውድ ዕቃዎች፣ ይዋቡባቸው የነበሩ አልባሳት፣ የከበሩ ንዋየ ቅድሳት፣ ነገሥታቱ በስጦታ ያበረከቷቸው ታሪካዊ ስጦታዎች እንደሚገኙበት ወይዘሪት ዓለምሸት ነግራኛለች፡፡ ወደ አንኮበር እግሩ የደረሰ ሁሉ በከፍታ ላይ ያለውን፣ ከፍ ያለ ታሪክ የተሰራበትን ቤተ መንግሥት እያዬ የከበረውን ታሪክ ይማራል፡፡

ዋሻ ገብርኤል ፍልፍል ቤተክርስትያን፤ ሊቅ ማረፊያ፣ የአብዱረሡል ታሪካዊ ስፍራ፣ የወሰንሰገድ ቤተ መንግሥት ፍርስራሽ፣ የቁንዲ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስትያን፣ ወፍ ዋሻ የተፈጥሮ ደን፣ ጋጀሎ የባሩድ ማንጠሪያ ስፍራ ፣ መስጫ ማሪያም፣ አባ ጽጌ ብርሃን ዋሻ፣ መነኩሴ ዋሻ፣ አባ ህዝቀኤል ዋሻ፣ ሚጣቅ ተክለሃይማኖት ደብረ ፀሐይ የአንድነት ገዳም እና ሌሎች እጅግ የከበሩ ታሪካዊና መንፈሳዊ ስፍራዎችንም ይመለከታል፡፡ ከታሪካቸው ታሪክን ይጠጣል፣ ከመንፈሳቸው ሀሴትን ያደርጋል፡፡
በዚህች ውብና ታሪካዊት ሥፍራ አጠገብ ያቺ የሲራራ ንግድ የደመቀባት፣ የቀረጥ ክፍያ የታየባት፣ እስከ ዘይላ ድረስ የሚጓዙባት ቀደምቷ አልዩአምባም ትገባለች፡፡ አልዩአምባ እኒያ ብርቱ ነጋዴዎች የተመላለሱባት፣ ነግደውም ያተረፉባት ታሪካዊት ሥፍራ ናት፡፡ በአልዩአምባ ተቀምጦ ትናንትን እያስታወሱ፣ በአልዩአምባዎች ፍቅር እየታደሱ ይኖራሉ፡፡

ʺየኢትዮጵያን ነገር ታሪክ ስትቀምሩ
የእምዬን መነሻ አንኮበርን ጥሩ” የተከበረችውን ሀገር፣ የማትደፈረውን ምድር የኢትዮጵያን ታሪክ የሚቀምር ሁሉ አንኮበርን ይጠራታል፣ አንኮበርን በደማቅ ቀለም ይጽፋታል፣ አንኮበርን በልቡ መዝገብ ላይ ያሰፍራታል፣ እምዬ ምኒልክንና ከእሳቸው አስቀድመው የነበሩ አያሌ ነገሥታትን ያስብባታል፡፡ አንኮበር የአንድነት መንበር፣ አንኮበር የጀግኖች ሀገር፣ አንኮበር የመኳንንትና የመሳፍንቱ አድባር፡፡ ይሂዱ ይጎብኟት፣ የከበረውን ታሪክ ይወቁባት፡፡

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!