ʺየተክለ ሃይማኖት መናገሻ፣ የሊቃውንት መዳረሻ”

136
ባሕር ዳር: ሕዳር 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በጥበብ የሚኖሩ ሊቃውንት ይሰባሰቡባታል፣ በረቀቀ ጥበብ ይኖሩባታል፣ መጻሕፍትን ይመረመሩባታል፣ ምስጢራትን ያሜሰጥሩባታል፣ የአውራጃ ገዢዎች በአማሩ ፈረሶቻቸው ተቀምጠው፣ በፊትና በኋላቸው፣ በቀኝና በግራቸው በጦረኞች ታጅበው፣ አምረውና ተውበው ይገሰግሱባታል፣ ጎበዛዝቱ ጋሻና ጦራቸውን አሳምረው፣ ጎራዴና ዝናራቸውን አስውበው፣ ጠመንጃቸውን ወላውለው፣ በጦር ልብሳቸው ተውበው ይገቡባታል፡፡
ወይዛዝርቱ በሀገርኛ ጥበብ አምረው፣ በረጃጅም ሽንጣቸው ላይ ቀጭን መቀነታቸውን አዙረው፣ ባማረው ተረከዛቸው ላይ አልቧቸውን አሳምረው ይመላለሱባታል፡፡ ማርና ወተቱ፣ ጮማና ፍትፍቱ ሙሉ ነው፡፡ በረዶ የመሰለው ነጭ ጤፍ እየተጫነ ይመጣባታል፣ ካማሩት ላሞች የሚታለበው ወተት፣ ከእንስራው የሚንቆረቆረው ጠጅና ጠላ ይፈስስበታል፡፡
ሀገረ ገዢው በክብር ይቀመጡባታል፣ ከሊቃውንቱ ጋር እየተማከሩ፣ ከጦር አበጋዞች ጋር እየዘከሩ ሕዝብ ያሥተዳድሩባታል፣ ፍትሕ ጠይቀው ለሚመጡት ፍትሕ ይሰጡበታል፣ ፍርድ እንዳይጓደል፣ ደሃ እንዳይበደል አድርገው ይፈርዱበታል፡፡ ጥበብ የተገለጠላቸው ሊቃውንት የጥበብ ጅረት ያፈስሱበታል፣ እነርሱን እያለ ለሚመጣው ደቀ መዝሙር ከሚፈስሰው የጥበብ ውኃ ያጠጡታል፣ ዕውቀትን ይሰጡታል፡፡
ሳርን የተባሉ ደገኛ ባላባት ነበሩ፡፡ እኒህ ደገኛ ባላባት ሁለት ልጆች ነበሯቸው፡፡ ዝና እና መንቆረር የተሰኙ፡፡ የአንደኛው ልጃቸው ሥም ለከተማ መጠሪያነት አገለገለች፡፡ ይህችም የተመረጠች ሥም መንቆረር ነበረች፡፡ በዚያ ዘመን ደጅ አዝማች ተድላ ጓሉ እያሥተዳድሩ ነበር፡፡ ዘመኑም 1845 ዓ.ም ነበር፡፡ በዚያም ዘመን አንዲት ለታሪክ የታጨች ትንሽዬ መንደር ተመሠረተች፡፡ በዚህም ዘመን ቋረኛው ካሳ ዘመነ መሳፍንትን አሳልፈው፣ የተበታተነውን ሰብስበው፣ የደከመውን አጠንክረው፣ ግርማው እየቀለለ የመጣውን ዙፋን አክብደው እና ወደ አስፈሪነቱ መልሰው ኢትዮጵያን አንድ ያደርጉ ዘንድ ትግል ላይ ነበሩ፡፡
እሳቸውም ጎጃምን ያደላድሉ ዘንድ ወደ ጎጃም አቀኑ፡፡ ሀገር እያደላደሉ ድንኳን ጥለው በጎጃም ቆዩ፡፡ ሀገር አደላድለው ሲመለሱም እርሳቸው ድንኳን ጥለው የከረሙባት መንደር ከተማ ትሁን ብለው አዘዙ፡፡ ከተማም ኾነች ይባላል፡፡ ያችም ከተማ መንቆረር የተሰኘችው ትንሿ መንደር ነበረች፡፡
ዘመን ዘመንን እየገፋ መጣ፡፡ ያቺ ለታሪክ የተመረጠች ትንሿ ከተማ የጠቅላይ ግዛቱ ሀገረ ገዢዎች መቀመጫ ኾነች፡፡ አጼ ዮሐንስ ንጉሠ ነገሥት ተብለው በዙፋን ላይ ተቀምጠዋል፡፡ በጎጃም ክፍለ ሀገር ደግሞ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ነግሠዋል፡፡ የመናገሻ ሥፍራቸውንም በመንቆረር አድርገዋል፡፡ በዚህም ጊዜ ደብር መደበር ፈለጉ፡፡ ከቤተ መንግሥታቸው እየወጡ ጸሎት የሚያደርሱበት፣ ኪዳን የሚያስደርሱበት፣ ቅዳሴ የሚያስቀድሱበት በአቅራቢያቸው በሚገኝ ሥፍራ ደብር ደበሩ፡፡
የደበሩት ደብርም መልዕክተ አድባር ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ማርቆስ ነበር፡፡ ይህም ታላቅ ደብር ከተደበረ በኋላ መንቆረር ስሟን ለደብረ ማርቆስ አስረከበች፡፡ ለምን ንጉሡ በአዋጅ ስሟ ይቀየር ዘንድ አዝዘዋልና፡፡ ያቺ ቀደም ብላ የተመሠረተችው ከተማ ደብረ ማርቆስ ተሰኘች፡፡ ከተማዋም ከፍ እያለች ሄደች፡፡ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት በዘመናቸው ቤተ መንግሥት አሠሩ፡፡ በዚያ ቤተ መንግሥትም ያማረውን ሁሉ አደረጉ፡፡ በቤተ መንግሥቱ የእልፍኝ አስከልካዮች፣ የጦር አበጋዞች፣ የዓለም አጫዋቾች፣ የቤተ መንግሥቱ አገልጋዮች በደስታ ይኖሩበት፣ ሊቃውንቱ በክብር ይስተናገዱበት፣ ንጉሡም በሞገስ ይቀመጡበት ነበር፡፡ ንጉሡ ታላቅ ታናሹን የሚያከብሩና የሚወድዱ ነበሩና በቤተ መንግሥቱ ያመረ ደስታ ነበር፡፡
ይህች የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት መናገሻ፣ የሊቃውንቱ መዳረሻ የኾነች ደብረ ማርቆስ ተክለ ሃይማኖት በሰጧት ሥም ገነነች፡፡ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ንጉሠ ጎጃም ወከፋ ተብለው ሲያሥተዳድሩ ኖሩ፡፡ የእርሳቸው ዘመን አለፈ፡፡ በእርሳቸው አልጋም ልጃቸው ተተኩ፡፡ የአባታቸውን ቤተ መንግሥትም ጠበቁ፡፡ እርሳቸውም አለፉ፡፡ የደጅ አዝማች ፀሐይ እንቁሥላሴ ዘመንም ደረሰ፡፡ እሳቸውም የንጉሥ ተክለ ሃይማኖትን ቤተ መንግሥት አሳመሩት፡፡ ደጅአዝማች ፀሐይ ቤተ መንግሥቱ ግርማን እንዲላበስ አድርገውታል፡፡
ልብን በሐሴት የሚመላው የካህናቱ ዜማ ከማርቆስ አጸድ ሥር ይንቆረቆራል፣ በአጸዱ ዙሪያ የቆሙት ረጃጅም ዛፎች ምሥጋና የሚያደርሱ ይመስላሉ፣ በነፋስ እየተገፉ ጎመበስ ቀና ይላሉ፣ በቀስታ ያረግዳሉ፣ ከቅዱስ ማርቆስ አጸድ ሥር የሚንቆረቆረው የካህናቱ ዜማ ዝም ያለ ሲመስል የአብማ ማርያም ሊቃውንት በኅብረት ሲያዜሙ ይሰማሉ፡፡
እንባን የሚያመጣ ዜማ፣ ዓለምን የሚያስንቅ ዜማ፣ በተመስጦ ከሰማያ ሰማያት የሚያሻግር ዜማ፣ ሊቃውንቱ እየተቀባበሉ ያዜማሉ፣ ምዕመናኑ ነጫጭ እየለበሱ ይገሰግሳሉ፣ በአጸዱ ሥር ኾነው ፈጣሪያቸውን ይማጸናሉ፣ ሰላምና ፍቅር በምድር ይኾን ዘንድ ይጸልያሉ፡፡ ለሰላምና ለፍቅር ይተጋሉ፡፡ በተክለሃይማኖት አደባባይ የሚሰባሰቡት፣ የዚያን ዘመን ታሪክ እያሰቡ ዛሬን በፍቅርና በተድላ የሚያሳልፉት ሌላ ደስታን የሚሰጡ ናቸው፡፡
ያቺ የቀድሟ ታናሿ መንደር ዛሬ ላይ ታላቅ ከተማ ኾናለች፡፡ ደብረ ማርቆስ ገና ያልታዩ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ሥፍራዎች ያሏት ታሪካዊት ከተማ መኾኗን የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ወይዘሮ የውልሰው ወርቅነህ ነግረውኛል፡፡ ባላት የቱሪዝም ሃብት ልክ ያልተጠቀመች፣ በውስጧና በዙሪያዋ ያሉ መስህቦችን በአግባቡ ያላሳየች ከተማ ናትም ብለውኛል፡፡
የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ቤተመንግሥትን ጨምሮ ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናትን እና ሌሎች መዳረሻዎችን የያዘችው ከተማ መንፈስን የሚያድሱ ሃብቶች አሏት፡፡ የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ቤተ መንግሥት እድሳት እንደሚሻም ኀላፊዋ ነግረውኛል፡፡ ቤተ መንግሥቱን ለማስጠገንም የሚያስችል እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን እና ጥገናው የሚካሄድበት ንድፍ መውጣቱንም ኀላፊዋ ገልጸዋል፡፡ የጥገናው ሂደት ግን በሚፈለገው ፍጥነት አለመጀመሩንም ነግረውኛል፡፡ የወጣው ጥገና ንድፍ የጎጃምን ታሪካዊ ሥፍራዎች የሚያመላክት እና የሚገልጽ ኾኖ ተሠርቷል ነው ያሉኝ፡፡
ደብረ ማርቆስ ለጎብኚዎች ምቹ ትኾን ዘንድ እየሠሩ መኾናቸውንም ነግረውኛል፡፡ የረቀቀ ቅኔ የሚቀኙ ሊቃውንት የሚኖሩባት፣ ጥበብ አዋቂዎች የሚገኙባት ከተማ ናት – ደብረ ማርቆስ፡፡ አፈር ስኾን እያሉ የሚያጎርሱ፣ የታረዘን የሚያለብሱ ደጋጎች የሚኖሩባትን ከተማ ይጎብኟት፡፡ ወተትና ማር የከበባት፣ ነጭ ጤፍ የሚከባት፣ ስንዴና በቆሎ የሚገባባትን ከተማ ይመልከቷት፡፡
ደጋግ ሰዎችን ያገኙባታል፣ ጸጋና በረከትን ያዩባታል፣ ሀገር ወዳድ ጀግኖችን ያገኙባታል፣ የጣፈጠውን እየበሉ፣ የጣፈጠውን እየጠጡ የሚያምረውን ታሪክ ይዩ፣ በታሪኩም ኢትዮጵያን ይወቁ፡፡ ሀገርዎን ያድንቁ፡፡
ʺ ማኛ ጤፍ እንጀራ በወተት የራሰ
ጎጃም ገብቶ አይወጣም እሱን የቀመሰ” እንዳለ ከያኒው በወተት የራሰውን እንጀራ የቀመሰ፣ ከጠጁ የተጎነጨ፣ ከጮማው የጎረሰ ጎጃም ገብቶ አይወጣም፡፡ በጎጃም ሰማይ ሥር እየተመላለሰ ይኖራል እንጂ፡፡ በወተት የራሰ ማኛ ጤፍ እንጀራ ለመብላት፣ መንፈስዎን በሐሴት ለመሙላት ወደ ማርቆስ ማቅናት፡፡
ምስል: ከፋይል
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!