ʺዓለምን የሚያደምቁት ጥቁር ከዋክብት”

174
ነጭመደበኛ
ነጭመደበኛ
ባሕር ዳር: ሕዳር 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሰማይ ከዋክብት ነጫጮች ናቸው፣ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ብርሃንን ይፈነጥቃሉ፣ ልኩ የማይታወቀውን ሰማይ ያደምቃሉ፣ በምድርና በሰማይ መካከል ያለውን ሰፊ ሥፍራ ያስጌጣሉ፣ ምድርን እና ሰማይ በብርሃን ያስተያያሉ፣ ከደማቋ ጨረቃ ዙሪያ ተኮልኩለው ልዩ ደስታን ይሰጣሉ፡፡
ምሽቱ በጨረቃ ይደምቃል፣ በከዋክብት ይረቅቃል፣ ያሸበርቃል፡፡ ብዙዎች ከዋክብት እየናፈቁ በምሽት ይወጣሉ፣ አንገታቸውን ወደ ሰማይ አንጋጥጠው፣ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ከዋክብት እየተመለከቱ በደስታ ባሕር ውስጥ ይጠልቃሉ፣ ፍቅራቸውን ያጣጥማሉ፡፡ ከዋክብት ለሰው ልጅ ልዩ ስሜት፣ ልዩ ደስታ አላቸው፡፡
የሰማይ ከዋክብት ጥቁሩን ያበራሉ፣ ጨለማውን ይገፍፋሉ፣ ድንግዝግዝ ያለውን ያደምቃሉ እንጂ ጥቆሮች አይደሉም፡፡ ታዲያ ነጫጭ አብረቅራቂ ከዋክብት ባሉባት ዓለም ውስጥ ስለምን ጥቁር ከዋክብት ነው የምታወራው? ጥቁር ከዋከብትስ አሉ ወይ? ትሉ ይሆናል፡፡ አዎን ጥቁር ከዋክብት በሰማያት ሳይሆን በምድር አሉ፣ አዎን ጥቁር ከዋክብት ከጨረቃ አጠገብ ሳይሆን በሰዎች መካከል አሉ፡፡ አዎን ጥቁር ከዋክብት ዓለምን እያደመቋት፣ ለዓለም ደስታን እየሰጧት በምድር አሉ፡፡
በምድር ጥቁር የሜዳ ላይ ከዋክብት ተፈጥረዋል፡፡ በድንቅ ብቃታቸው የዓለምን ልብ ገዝተዋል፣ ስማቸውን ከፍ አድርገው ጽፈዋል፣ ለዓለምም ልዩ ደስታን ይዘው መጥተዋል፡፡ የፍቅር ግጥሚያ ባለበት ሜዳ ውስጥ ከዳርዳር ያበራሉ፣ ሜዳውን እያካለሉ፣ በዙሪያ ገባቸው የተኮለኮለውን ሕዝብ በደስታ ይንጣሉ፡፡ እነርሱን የሚያዩ በደስታ ያነባሉ፣ ወደር በሌለው ደስታ ውስጥ ኾነው ይዘምራሉ፣ ይደልቃሉ፡፡
ለወትሮው ጨዋታ ከቁም ነገር አይቆጠርም ነበር፡፡ ጨዋታ ሥራ እንደመፍታት ይቆጠርም ነበር፡፡ ዛሬ ግን ዓለም ጨዋታን ሥራዋ አድርገዋለች፣ ጨዋታን ሥራቸው ያደረጉ ከዋክብትም ዓለሙን በዝና ናኝተውበታል፣ ለቁጥር የሚያታክት ገንዘብ ቆጥረውበታል፣ በጨዋታ ደምቀውበታል፣ በጨዋታ ክብር አግኝተውባታል፡፡ ዛሬ ጨዋታ የገንዘብም የደስታም ምንጭ ኾኗል፡፡ ዓለም በተጨነቀችበት ዘመን የእግር ኳስ ጨዋታ የተፈጠረላት ይመስላል፡፡ እግር ኳስ የብዙዎች የደስታ እና የሃብት መሠረት እየሆነ ከመጣ ሰነባብቷል፡፡
ስለ እግር ኳስ ሳይነገር የዋለበት ቀን ያለ አይመስልም፡፡ በወጎች መካከል እግር ኳስ ይነሳል፡፡ ስለ እግር ኳስ ይወሳል፡፡ አሁን ጨዋታ ጀግኖች የሚፈጠሩበት፣ አርዓያ ያላቸው ከዋክብት የሚወጡበት፣ የጥንካሬ ምሳሌ የሆነ ጀግኖች የሚገኙበት፣ ዓለም የሚነጋገርባቸው፣ ለዓይን የሚጓጓላቸው፣ ታሪካቸውን ለመስማት ጆሮውን የሚያዘነብልላቸው ፈርጦች የሚገኙበት የትግል አውድ ኾኗል፡፡ ከእነዚህ ከዋክብት መካከል ጥቋቁር ከዋክብት የሜዳው ድምቀት ኾነው ዓመታትን ተሻግረዋል፡፡ ጥቋቁር ከዋክብት ዓለምን እያደመቋት፣ ከጭንቀትና ከሃዘን እያራቋት፣ ደስታን እየለገሷት ነው፡፡
ዓይኖች ሁሉ ያዩት ዘንድ የሚመኙት፣ ጀሮዎች ሁሉ ለመስማት የሚያዘነብሉለት፣ አንደበቶች ሁሉ የሚናገሩለት፣ ስለ ታሪኩና ስለሚፈጠረው ክስተት ያለ ማቋረጥ ብዕርና ብራና የሚገናኙበት፣ አንደኛው ኮከብ ከሌላኛው ኮከብ ደምቆ ለመታየት የሚታገልበት፣ የሜዳ ላይ ጦርነት የሚካሄበት፣ ብዙዎች በፍቅር የሚዋኙበት የዓለም ዋንጫ ሠርግ ዋዜማ ላይ ነን፡፡
ባለ ጠጋዋ ኳታር ድግሱን ደግሳለች፣ ጎዳናዎቿን አሳምራለች፣ ለእንግዶቿ ማረፊያ የሚሆነውን የተንጣለለ አዳራሽ አዛጋጅታለች፣ ድግሡ የሚደገስበትን ሜዳ አስውባለች፣ ድግስ ደግሳ ዓለማት ሁሉ የሚያዩት፣ ዓለማት ሁሉ የሚደሰቱበት ሠርግ ሠርጋለች፡፡ ይሄን የመሰለ ሰርግ ለማሥረግ መመረጥ ነው፤ ለምን ሕዝብ ሁሉ ይጓዝባታል፣ ዓይኖች ሁሉ ያዩዋታል፣ የመገናኛ ብዙኃን ሁሉ ያወሩላታልና፡፡ የሰርጉ ቀን ሊጀመር፣ የሀገራት መዝሙር ከዳር ዳር ሊዘመር፣ ከዋክብቱ ሊፋለሙ፣ ደጋፊዎች በስታዲዬም ሊታደሙ ተቃርቧል፡፡
የዓለም ዋንጫ ድግስ አሃዱ ካለበት፣ ድግሡ ከተጀመረበት ከደቡብ አሜሪካዊቷ ኡራጋይ አሁን እስከ ደገሰችው ኳታር እስከሚደርስ ድረስ አያሌ ታሪኮች ታይተዋል፡፡ አይረሴ ክስተቶች ተመዝግበዋል፤ ድንቅ የሆኑ ከዋክብት አልፈዋል፡፡ የማይረሱ የደስታ ምሽቶች፣ ልብ የሚሰብሩ የሐዘን አጋጣሚዎችም የዚሁ አንድ አካል ናቸው፡፡ በሜዳ ላይ ነግሰው የድግሱን የመጨረሻ ክብር የሚሸለሙት ከዳር ዳር በደስታ ሲዘምሩ፣ የድግሱን የመጨረሻ ክብር የተነጠቁት የእንባ ማዕበል ሲተናነቃቸው ማየትም የተለመደ ነው፡፡ በአንድ ሜዳ ሐዘን እና ደስታ ይታያሉ፣ አሸናፊና ተሸናፊ ይገኛሉ፣ ሳቅና ለቅሶ ይቀላቀላሉ፡፡ የዓለም አሳዛኟንም አስደሳቿንም ገጽ ያሳያሉ፡፡
በእነዚህ አስገራሚ ታሪኮች ውስጥ ልቀው የሚወጡ ጥቋቁር ከዋክብት አሉ፡፡ ጥቋቁር ከዋክብት በሜዳው ላይ ይነግሳሉ፣ በሜዳው ላይ ይደምቃሉ፣ የመጨረሻውን የክብር ሽልማት ይዘው ይሸለማሉ፡፡ የዓለም ዋንጫ አያሌ ጥቋቁር ከዋክብትን አሳይቶናል፡፡ አያሌ ጥቋቁር ጀግኖችን አስመልክቶናል፡፡ የእነዚህ ጥቋቁር ከዋክብት መፍለቂያና፣ መገኛ ደግሞ የጥቁሮች ምድር አፍሪካ ናት፡፡May be an image of 5 people and people standing
ታዲያ የበዙት ጥቋቁር ከዋክብት፣ የዘር ሀረጋቸው ከሚመዘዝባት፣ ማንነታቸው ከሚቀዳባት አፍሪካ ርቀው በስደት ለተወለዱበት ሀገር ይጫዋታሉ፡፡ በዚያ ባደጉበት ሀገር ተሰልፈው በዓለም ፊት ይደምቃሉ፣ ብዙዎች የሚመኙትን፣ በዘመናቸው ሁሉ ሊያሳኩት የሚሹትን የዓለም ዋንጫ ክብር በስደት ለኖሩበት ሀገር ያስረክባሉ፡፡ እነርሱ የዘር ሀረጋቸው የተመዘዘባት፣ ጥቁሮች የሚፈልቁባት አፍሪካ ግን ለክብር ሳትታደል ትቀራለች፡፡
ዘሩ ከአፍሪካ የሚመዘዘው ዚዳን ፈረንሳይን በዓለም አንግሷታል፣ ከፍ ከፍም አድርጓታል፣ ፈረንሳይን በእግሮቹ ጥበብ አንድ አድርጓታል፣ የእርሱን ወላጆች ያስገኘች አፍሪካ ግን በዓለም ዋንጫ አልነገሰችም፡፡ እርሱን የሰጠች አፍሪካ ግን በዓለም ዋንጫ አልደመቀችም፡፡ ለወርቁ ዋንጫ አልታደለችም፡፡ የእርሱ አልጋ ወራሾች፣ ፖል ፖግባ፣ ኒጎሎ ካንቴ እና ሌሎች ጥቋቁር ከዋክብት ፈረንሳይን ዳግም በዓለም ላይ አነገሷት፡፡ በጥበባቸው ዓለምን አደመቋት፡፡ የእነርሱ መነሻ የሆነች አፍሪካ ግን በዓለም ላይ መድመቅ አቃታት፡፡ በወርቅ የተንቆጠቆጠው ዋንጫ ራቃት፡፡May be an image of 6 people and people standing
የዘር ሀረጋቸው ከአፍሪካ የሚመዘዙ ጥቋቁር ከዋክብት የዓለምን እግር ኳስ አሳምረውታል፡፡ የዓለም ዋንጫውንም አድምቀውታል፡፡ ከአፍሪካ ሀገራት እየተነሱ ወደ ሌሎች ሀገራት እየተጓዙ ሌሎች ሀገራትን ባለ ክብር አድርገዋቸዋል፡፡ እናታቸው አፍሪካ ግን የዓለም ዋንጫን እንደተራበች ዓመታትን አሳልፋለች፡፡ አፍሪካን እየወከሉ በዓለም አደባባይ የሚገኙ የአፍሪካ ሀገራትም የመጨረሻውን የድል ዋንጫ መያዝ ሳይችሉ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡
ዓለም ግን አሁንም በጥቋቁር ከዋክብት ትደምቃለች፣ በጥቋቁር ከዋክብት ፊታውራሪነት ትመራለች፣ ለዓለም ዋንጫ ድል የሚገመቱ ሀገራት በውስጣቸው ጥቋቁር ተጨዋቾችን ይዘዋል፣ በጥቋቁር ከዋክብት አሸብርቀዋል፡፡ አፍሪካን ወክለው እስከመጨረሻዋ የላብ ጠብታ ድረስ የሚፋለሙ ጥቋቁር ከዋክብትም ሞልተዋል፡፡ ዘንድሮም ጥቋቁር ኮኮቦች ቀናት በቀሩት የኳታሩ የዓለም ዋንጫ ይደምቃሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የጥቋቁር ከዋክብት መገኛ አፍሪካ ከዋክብትን ለዓለም ብትሰጥም፣ ብዙዎች የሚሳሱለትን የወርቅ ዋንጫ ግን የሰጣት የለም፡፡ ለዚያ ክብር አልታደለችም፡፡ ከቀናት በኋላ በኳታር የሚጀምረው ግዙፉ ድግስ የትኛውን ሀገር ባለ ድል ያደርግ ይሆን? ቀናት መልስ ይኖራቸዋል፡፡ በዚያች በመጨረሻዋ ቀን የአሸናፊዋ ሀገር ደጋፊዎች በደስታ ሲነግሡ፣ የተሸናፊዋ ሀገር ደጋፊዎች በሐዘን ሲያለቅሱ የሚታይበትን ቀን ብዙዎች ይጠብቁታል፤ ለማየትም ይጓጉለታል፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!