ʺቢያወጣልኝ ብሎ የፍቅሩን ትኩሳት፣ የጋፋትን አፈር አቀለጠው በእሳት”

0
179

ባሕር ዳር: ሕዳር 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ቴዎድሮስ ኾይ የሀገር ፍቅሩ እስከ ምን ድረስ ነው? ቴዎድሮስ ኾይ የጽናት ጥጉ እስከ የት ነው? ቴዎድሮስ ኾይ የክብር መገለጫው ምንድን ነው? ቴዎድሮስ ኾይ ለክብር መሞት፣ ለሀገር ፍቅር ጠጅ በተጠጣበት ጉሮሮ ባሩድ መጎንጨት፣ እንዳሸነፉ ኖረው አሸንፈው መሞት የሚቻለው እንድምን ነው? ቴዎድሮስ ኾይ ጀግንነትን፣ ሀገር ወዳድነትን፣ አንድነትን፣ አትንኩኝ ባይነትን፣ ባለ ራዕይነትን በአንድ ላይ መያዝ የሚቻለውስ እንዴት አድርጎ ነው?
ከእናቱ እግር ሳይጠፋ ገና ሀገሩን ወደዳት፣ ሀገሩን በእናቱ ፊት ላይ አያት፣ እናቱ እንድያ ልጇን በምትወደው ልክ እርሱም አንዲት ሀገሩን ወደዳት፣ እንደ እናቱ አከበራት፣ እንደ እናቱ የክብሯን ቀሚስ ጨብጦ ተከተላት፣ አሜካለውን እየቀደመ ጠረገላት፣ የሚገባትን ክብር፣ የሚመጥናትን ፍቅር ሰጣት፣ ሀገር ማለት እናት፣ እናት ማለት እትብት አለ፡፡ የታደሉት አንድ ኾነው ተፈጥረው እንደሺህ ይኖራሉ፣ በጨለማ ዘመን ተገኝተው የዘመን ብርሃን ይኾናሉ፣ መንገድ የጠፋበትን መንገድ ያሳያሉ፣ ክፉውን ዘመን በጥበብ መርተው ያሻግራሉ፡፡ ዘመን የማይሽረው፣ ታሪክ የማይረሳው ታሪክ ቀርጸው ያልፋሉ፡፡ እርሱ አንድ ኾኖ በቀለ እንደ ሺህ ኖረ፣ እርሱ ጥቂት ዘመን ኖረ፣ የሺህ ዘመን መስመር አሰመረ፡፡ እርሱ ጥቂት ዘመን ኖረ የሺህ ዘመን ቃል ኪዳን አሠረ፡፡

ዙፋኑን ወደ አስፈሪ ግርማ ሞገሱ መለሰው፣ የደከመውን መንግሥት አበረታው፣ ኢትዮጵያን አብዝቶ ወደዳት፣ ከልጅነት እስከ ሞት ድረስ ለፍቅሯ ተንከራተተላት፣ ለፍቅሯ ሲል ሞትን ናቀላት፣ ለክብሯ ሲል ወደቀላት፣ ለፍቅሯ ሲል በሞቱ አከበራት፣ በሞቱ አኮራት፣ በሞቱ አስጠራት፡፡ ባለ ራዕዩ ንጉሥ ገና በልጅነት ዘመኑ ራዕይ ታጠቀ፣ ከዘመኑ የቀደመ ጥበብ ሰነቀ፡፡
በእርሱም ዘመን፣ ከእርሱም ዘመን በኋላ ቴዎድሮስ፣ ቴዎድሮስ እየተባለ በክብር ተጠራ፡፡ ራዕይ ታጥቆ ተነስቷል፣ ራዕዩን እውን ያደርግ ዘንድ ታትሯልና ትውልድ ሁሉ ያከብረዋል፡፡ በስሙ ይማልበታል፣ በክብሩ ይኮራበታል፣ ባሰመረው መሥመር ትውልድ ይጓዝበታል፡፡ ቴዎድሮስ አባቶቹ ባሠሩት ቤተ መንግሥት፣ የወርቁን በትር ጨብጦ፣ ከአማረው ዙፋን ላይ ተቀምጦ፣ የእልፍኝ አስከልካዮች፣ ዓለም አጫዋቾች፣ የጦር አበጋዞች፣ መኳንንቱና መሳፍንቱ እጅ እየነሱለት መኖርን አልወደደም፡፡

የሚወድዳት ሀገሩን ከፍ ያደርጋት፣ በጠላቶቿ ዘንድ ግርማ ሞገስን ያላብሳት፣ ከእነ ክብሯና ከእነ ማረጓ ያኖራት ዘንድ ያለ ድካም በአውራጃዎቿ ሁሉ ተመላለሰ፡፡ በድንኳን እያደረ ሀገሩን ለማቅናት ደከመ፡፡

ጠላቶች የሚበዙባት ሀገሩ ኢትዮጵያ ለዘላለም ተከብራ ትኖር ዘንድ እንደርሱ አይነት ባለ ራዕይ ንጉሥ፣ እንደ ገብርየ ያለ ጀግና እና ታማኝ የጦር መሪ ባለባት ሀገር ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቁ ጀግና የሚመራቸው፣ ጀግና ወታደሮች ይኖሩት ዘንድ ግድ መኾኑን አሰበ፡፡ ራዕዩን አውን ያደርግ ዘንድም ቆርጦ ተነሳ፡፡ ቴዎድሮስ በዘመናዊ የጦር መሳሪያ እየታገዙ አብዝቶ የሚወዳትን ሀገሩን ለመውረርና ለመድፈር የሚመኙ ጠላቶች መበርከታቸውን አውቋል፡፡ በሀገሩ ወደር የማይገኝለት ጀግንነት፣ እስከ ሞት ድረስ የሚልቅ ሀገር ወዳድነት እንዳለም ያውቃል፡፡ ታዲያ ጀግነቱን የሚያግዝ፣ ሀገር ወዳድነቱን የሚደግፍ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ይኖር ዘንድ ግድ ነው አለ፡፡
እርሱ የታጠቀውን ወንድነት እና ጀግንነት ጠላቶቹ እንደማይታጠቁት ያውቃል፡፡ እነርሱ የታጠቁትን ዘመናዊ መሳሪያ መታጠቅ እንደሚችልም አመነ፡፡ በሀገሩም የጦር መሳሪያ ለማምረት ታተረ፡፡ የጦር መሳሪያ ይመረትባት ዘንድ የተመረጠችው፣ የቴዎድሮስን ራዕይ እውን ይሆንባት ዘንድ የታጨችው ደግሞ የጠቢባን ቦታ ጋፋት ነበረች፡፡ ጋፋት የቴዎድሮስ የዘመን ብርሃን የበራባት፣ የቴዎድሮስ ራዕይ እውን መኾን የጀመረባት፣ በራስ ሀገር ሁሉንም መስራት እንደሚቻል የታየባት፣ በኋላም ቴዎድሮስ ተስፋውን፣ ራዕዩን፣ ቃል ኪዳኑን፣ የሀገር ፍቅሩን፣ ዘምኖ የማዘመን ጉጉቱን፣ ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ ለተጎዱት ሀገራት የመድረስ ሕልሙን ሁሉ ያስቀመጠባት ሥፍራ ናት፡፡


በጋፋት ቴዎድሮስ ያስቀመጠው አደራ፣ ራዕይ፣ ጥበብ፣ ቃልኪዳን፣ ተስፋና የሀገር ፍቅር አለ፡፡ ጋፋት የጠቢባን መንደር፣ ጋፋት የራዕይ መተግበሪያ፡፡ በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የአለቃ ገብረሃና የባሕል ጥናት ዳይሬክተርና የታሪክ መምህሩ መሠረት ወርቁ ጋፋት የቴዎድሮስ ራዕይ እውን መኾን የታየበት፣ ለዘመናዊት ኢትዮጵያ መገለጫ የኾነው አርማ ያለባት ናት ይላሉ፡፡ ጋፋት በአፍሪካ ከሚጠቀሱ ጥንታዊ የብረታ ብረት ማምረቻ ሥፍዎች መካከል አንዷ መኾኗንም ነግረውኛል፡፡

ጋፋት የእደ ጥበብ ሥራ ወደ ኢንዱስትሪ ያደገበትና ማዕከል የሆነበት ሥፍራ ናት፡፡ ቴዎድሮስ ከችግር መፍትሔ የሚወልድ፣ ከዝቅታ ከፍታን የሚያስብ፣ ዛሬ ላይ ነገን የሚቀምር መሪ መኾኑንም ነግረውኛል፡፡

የተደራጀ፣ ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀ እና በአንድ የእዝ ሠንሰለት የሚመራ ሠራዊት እንዲኖረው ከመፈለጉ የተነሳ ብዙ ታትሯል፡፡ ደሞዝ የሚቆረጥለት፣ በሥነ ምግባር የታነጸ እና የእዝ ሰንሰለት የሚከበርበት ሠራዊት መፍጠር የቴዎድሮስ ዓላማና ሥራም ነበር ነው ያሉኝ፡፡ ቴዎድሮስ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ለማምረት የጠቢባን መንደር ጋፋትን በብዙ መመዘኛ መርጧታል፣ የሚፈለገውን አፈር የያዘች፣ የብረት ማቀዝቀዣ ውኃም ያለባት በመሆኗ ጋፋት ተመረጠች፡፡

ቴዎድሮስ በጋፋት ሥራ ካስጀመረ በኋላ ሥሩ ብሎ ዝም አላላም ነበር፣ ጠቢባንን እየተመላለሰ ያበረታቸው፣ ሥራቸውንም ያይም ነበር፡፡ ቴዎድሮስ በጋፋት ሴቫስቶፖል ማሰራቱንና በተሰራለት ጊዜም ደስተኛ መኾኑን ነግረውኛል፡፡ ዘመናዊ ጦር መሳሪያ፣ ዘመናዊ የሠራዊት ግንባታ የተገበረው ታላቁ ንጉሥ ወደ ሀገሩ የመጣውን ጠላት ጋፋት ላይ ባሠረው መሣሪያ ለመመከት ታላቅ ነገርን አደረገ፡፡ ቴዎድሮስ ጋፋት መንገድ ቆሞ የሚያሠራ መንገድ መሪው እየተባላ እንደሚጠራም መምህር ወርቁ ነግረውኛል፡፡
በቴዎድሮስ ራዕይ ላይ የተመሠረተውና የቴዎድሮስን ሥራ አርማ ያደረገው የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የቴዎድሮስን ጥያቄዎች ለመመለስ፣ የቴዎድሮስን ራዕዮች እውን ለማድረግ እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የቴዎድሮስን ራዕይ እውን ለማድረግ እንደ ቴዎድሮስ አርቆ የሚያስብ፣ ሀገሩን የሚወድድ፣ ከድክመቱ የሚማር ተማሪ ማፍራት አንደኛው ጉዳይ መኾኑን ነው የነገሩኝ፡፡
የጋፋት ኢንዱስትሪ መንደርን ማስከበር የመጀመሪያው ሥራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ታላቁን ሥፍራ እያስከበረ መሆኑንም አንስተዋል፡፡ የደብረ ታቦር፣ የጎንደር እና የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ባለሙያዎች ሥፍራው የቀደመውን መልክ እንዲይዝ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመራቸውንም ገልጸዋል፡፡ ጋፋትን ሊገልጽ የሚችል እና የቀደመውን የሚያስታውስ እደ ጥበብ መሠራት እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡ ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ በጋፋት የተሰየመ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ለመመስረት እየተንቀሳቀሰ እንደሆነም ነግረውኛል፡፡ የቴዎድሮስን ዘርፈ ብዙ እውቀት እውን ማድረግ የሚያስችል ሥራ መስራት እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

ጎብኚዎች ጥንታዊቷን ደብረ ታቦርን፣ የራዕይ እውን መኾኟን ጋፋትን እንዲጎበኙም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ደብረ ታቦር ታላላቅ ታሪኮች ያሉባት እና በዙሪያዋ የበዙ ታሪካዊና መንፈሳዊ ሥፍራዎች የከበቧት ከተማ ናትና፡፡ ጋፋትን በማየት እንዴት ራዕዩን እንተግበረው ማለት እንደሚገባም ተናግረዋል፣ ጋፋት ለሀገር ነብሱን ጭምር የሰጠ፣ አንድ የሚያደርግና የመነሳት ምልእክት የኾነ መሪ የነበራት ታላቅ ሥፍራ ናት፡፡

ʺቢያወጣልኝ ብሎ የፍቅሩን ትኩሳት፣
የጋፋትን አፈር አቀለጠው በእሳት” እንዳለች ዘፋኟ ቴዎድሮስ የፍቅሩን ትኩሳት ያወጣበት፣ የፍቅሩን ልክ ይገልጥበት፣ ራዕዩን እውን ያደርገበት ዘንድ የጋፋትን አፈር በእሳት አቀለጠው፡፡ በጋፋት ጥበብን ፈለጋት፣ ጥበብን መረመራት፣ በጋፋት ራዕይን አሰሳት፡፡ አዎ እርሱ ከምንም በላይ ሀገሩን ያፈቅራል፣ ነብሱን ሳይቀር በፍቅር ይሰጣል፡፡ ሂዱ ጋፋትን ተመልከቷት፣ ቴዎድሮስ ያሰቀመጣትን ራዕይ ያንሷት፣ ሂዱ ጋፋትን አስሷት የቴዎድሮስን የጥበብ ምስጢር ፍቷት፤ ወደ ጋፋት ገስግሱ ቴዎድሮስ ያስቀመጠውን ፍቅር፣ ተስፋ፣ ራዕይ እና ጀግንነት አንሱ፡፡

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!