ʺለአማራ ሕዝብ የምናስብ፣ የምንቆረቆር፣ የአማራ ሕዝብ ሕመም የሚያመን ከሆነና የአማራን ጥንተ ተጋድሎ የምናውቅ ከሆነ በአንድነት መቆም አለብን” ዶክተር ዘመነወርቅ ዮሐንስ

0
58

ባሕር ዳር: የካቲት 03/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ሠንደቁን የሚያክብር፣ በጀግንነት የሚኖር፣ ታሪክ የሚዘክር፣ ወገን የሚያፈቅር፣ ለጠላት የማይበገር ነው አማራ፡፡ ሀገር ለማጽናት፣ የዘመመውን ለማቅናት በየዘመናቱ አያሌ መስዋእትነት ከፍሏል፡፡ ኢትዮጵያን የሚጠሉ ጠላቶች ታዲያ ተቀዳሚ ጠላታችን ነው በማለት በደል ፈጽመውበታል፡፡ አሁንም እየፈጸሙበት ይገኛሉ፡፡ ደም አፍስሶ አጥንት ከስክሶ ባቆማት ሀገሩ በሰላም እንዳይኖር የሚያዋክቡት ብዙዎች ናቸው፡፡
በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ተመራማሪ ዶክተር ዘመነወርቅ ዮሐንስ እንዳስረዱት ኢትዮጵያ ከፍ ብላ እንድትጠራ የአማራ ሕዝብ ሚና የላቀ ነው፤ ጀግኖች አባቶች ሀገር ሀገር እንድትሆን አድርገዋል፡፡ በእግራቸው ተጉዘው፣ አድካሚውን ዘመን አልፈው ታላቅ ሀገር መሥርተዋል፤ ከሌሎች ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን ኢትዮጵያ የአሸናፊዎች ሀገር ኾና እንድትጠራ አበርክቷቸው ላቅ ያለነ እንደነበረም ነው ያነሱት፡፡
ተመራማሪው የአማራ ሕዝብ በእግሩ ከቦታ ቦታ እየተንከራተተ፣ ትጥቅና ስንቅ ከቤቱ እያወጣ፣ መድኃኒት እየቀመመ፣ እናት ሀገር ኢትዮጵያን ሀገር ያደረገ ጀግና፣ ደግና ኩሩ ሕዝብ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ ስትከፋ የሚከፋው፣ ኢትዮጵያ ስትታመም የሚያመው የእውነት ስለሚወዳት ነውም ብለውኛል፡፡ ኢትዮጵያ ሀገር ኾና እንድትቆም ከሌሎች ሀገር ወዳድ ወንድሞቹ ጋር በመሆን ዋጋ የከፈለላት፣ በደምና በአጥንቱ በማይናወጽ መሠረት ላይ ያቆማት ናትም ነው ያሉት፡፡
የአማራ ሕዝብ ለሀገር የከፈለውን ዋጋ እንደዚህ ነው እንደዛ ብሎ መግለጽ እስከሚያስቸግር ድረስ ዋጋው የረቀቀ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የአማራ ሕዝብ የማንንም ክብር እንደማይነካ የገለፁት ምሁሩ የኢትዮጵያን አጥር የሚነካበት፣ ክብሯን የሚደፍርበት ከመጣ ግን ማንንም እንደማይታገስና እስከ ሕይዎት ፍጻሜ ድረስ እንደሚታገል ነው ያብራሩ፡፡
ለኢትዮጵያ ቀናዒ ከሆኑ ኢትዮጵያውያን ጋር ደሙን አፍስሶ፣ ስጋውን ቆርሶ ባጸናት ሀገሩ ላይ ምንም ቢመጣ ድርድር ውስጥ እንደማይገባ ነው ምሁሩ ያስረዱት፡፡
ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ባልነበረበት ዘመን በራሱ መጓጓዣ እና መንገድ እየተጓዘ ሀገር አጽንቷልና በዚህ ዘመንም ኢትዮጵያን እናፍርሳት ለሚሉትም በፍጹም አይፈቅድም፡፡ ለውጭና ለውስጥ ጠላቶች እንቆቅልሽ እስኪሆን ድረስ ዋጋ ከፍሎ፣ እምቢ ለሀገሬ የሚለውን የአባቶቹን ብሂል ይዞ ሀገር እያስከበረ ያለ ሕዝብ ነው አማራ፡፡
ኢትዮጵያ በአስተማማኝ መሠረት ላይ እንድትቆም፣ የማይናወጽ መሰሶ እንዲኖራት እልፍ ጀብዱዎችን ፈጽሟል፤ በመፈጸምም ላይ ነው፡፡
አማራ ኢትዮጵያን በስጋዊ አውድ ብቻ አይደለም የሚረዳት፤ በአጸደ ነብስም ተከትላቸው ሄዳ እነዚህ ልጆቼ ዋጋ የከፈሉልኝ ናቸው እንድምትላቸውና የነብሳችን ዋስ ጠበቃ ናት ብለው የሚያምኑ ናቸውም ይላሉ ምሁሩ፡፡ ከስጋዊ ዓለም ባለፈ እስከ ሰማያዊ ዓለም ተከትላቸው የምትሄድ ማሕተማቸው አድርገው የሚቆጥሯት፣ እርሷ ለእነርሱ፣ እነርሱ ለእርሷ የሚኖሩላት ትልቅ ምስጢር ነው ያላቸው ሲሉም ይገልጻሉ፡፡ ሌሎች ለኢትዮጵያ ቀናኢ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያ እልፍ መስዋእትነት መክፈላቸውንም ነግረውኛል፡፡
የታሪክ ተመራማሪው እንዳብራሩት ኢትዮጵያ የዓለም ፈርጥ ኾና እንድትቀጥል፣ ዓለማት እንዲገረሙባት የማይታመን የሚመስል ጀብዱ የፈፀሙ ጀግኖች እልፎች ናቸው፡፡ የአማራ ሕዝብ በኢትዮጵያ ጉዳይ ከማይደራደሩ፣ ከእርሷ በፊት እኔ ልውደቅላት ከሚሉ ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን አጽንቷታል፤ ለቀኝ ግዛት እንቢ ያለ፣ ለጥቁሮች መልካም ዘመን ያመጣ ጀግና ሕዝብ ነው አማራ፡፡
ኢትዮጵያ ሁልጊዜ አሸናፊ ናት፤ ኢትዮጵያን ያሉ ሁሉም አሸናፊዎች ናቸው፤ ኢትዮጵያ በየዘመናቱ ለእርሷ የሚሞትላት ልጅ አታጣም፡፡ በሕልውና ዘመቻው የዓለም ሀገራት የሽብር ቡድኑ ድል እንደሚቀዳጅ ተስፋ ቢያደርጉም ሊያምኑት በሚያስቸግር መንገድ የአማራ ሕዝብና ሌሎች ኢትዮጵያውያን የጠላቶችን ሕልም መና ማድረጉንም አንስተዋል፡፡
ታሪክን በእውነተኛው አውድ ለሚረዳ የዓለም ማሕበረሰብ እንቆቅልሽ የሆኑ ልጆች ያሏት እንቆቅልሽ የሆነች ሀገር መኾኗንም ዶክተር ዘመነወርቅ ገልጸዋል፡፡
የአማራ ሕዝብ ሀገር በምን መንገድ እንደቆመች ያውቀዋል፤ ድካሙ ይገባዋል፤ ለዚያም ነው ከአንቺ በፊት እኔ ልውደቅልሽ የሚለው ብለዋል ዶክተር ዘመነወርቅ፡፡
ሥርዓት አዋቂና አክባሪ የሆነው የአማራ ሕዝብ መንግሥት ያለውን እያከበረ እንጂ ጦርነቱ አሁንም እንዳላበቃ ያስታወሱት የታሪክ ምሁሩ ጠላቶቹን ነቅሎ መጣል እንደሚችልም ገልጸዋል፡፡
የአማራና የአፋር ሕዝብ አሁንም ችግር ላይ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ ጠላቶች እንድንበታተን ይፈልጋሉ፤ መለያዬት ግን የጠላትን አጀንዳ ማስፈጸም ነው ብለዋል፡፡
የአማራና አፋር ሕዝብ ለምን ፈተናው በዛባቸው? ተብሎ ሲጠየቅ ጠላት በኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ፣ የጦር ሜዳ አርበኛ አማራ ነው የሚል ቅስቀሳ ነበረው፡፡ ሀገር ሀገር እንድትሆን አያሌ መስዋእትነት ከፍሏልና እርሷን ሲነኩበት አይደራደርም፤ ይህ ባሕሪው ደግሞ ለጠላቶቹ አይመችም፡፡ አፋርም ኢትዮጵያን ለመድፈር የመጣውን ጠላት ድባቅ መትቶ የመለሰ ጀግና ሕዝብ ነው፤ ኢትዮጵያን ለማፍረስ እነዚህ ሕዝቦች መጥፋት አለባቸው የሚለው የጠላት ቅዠት ለአማራና ለአፋር ችግሩ እንዲበረታባቸው ማድረጉን ነው ምሁሩ የገለጹት፡፡
የአማራ ሕዝብ ስርዓት አዋቂ ፣ ለሥርዓተ መንግሥት ተገዢ የሆነ ጀግና ሕዝብ ነው፡፡ “ለአማራ ሕዝብ የምናስብ ፣ የምንቆረቆር፣ የአማራ ሕዝብ ሕመም የሚያመን ከሆነና የአማራን ጥንተ ተጋድሎ የምናውቅ ከሆነ በአንድነት መቆም ይገባናል” ነው ያሉት፡፡
ተመራማሪው እንዳነሱት የመከፋፈል መንገድ አያዋጣም፤ ራሳችንን ነው ሰለባ የሚያደርገን፤ እናም ለጠላት ሰለባ በምንሆንበት መንገድ መጓዝ የለብንም፡፡ የአማራ ጥንተ ታሪክና ተጋድሎ አንድነትና አንድነት ብቻ ስለነበር ጽንፍ የረገጠውን ሐሳብ በመተው ለአማራ ሕዝብ ሕመሙን በአንድ ቋንቋ ልንናገርለት፣ ልንገልጽለት የሚገባን ጊዜ አሁን ነውም ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
ተመራማሪው እንዳሉት የሚታየው ነገር ላይመቸን ይችል ይኾናል፤ ነገር ግን የሚቀድመው የጋራ ጠላትን በጋራ ማጥፋትና በጋራ ቀና ማለት ነው፤ መሳሳቡ አይጠቅምም፤ መከፋፈል የጠላትን ሃሳብ ማስቀጠልና የእርሱ ተባባሪ መሆን ነው፡፡ የአማራ ሕመም የሚያመን ከሆነ ተናበን ለአማራ የሚጠበቅብንን መስዋእትነት መክፈል እንደሚገባ ነው የጠቀሱት፡፡ መከፋፋል መከራ አብዝቷል፤ አንድነት ግን በታሪክ አዲስ ታሪክ አምጥቷል ብለዋል።
አንድነት ዋጋ አለው፤ አንድነት እውነት ነው፤ አንድነት አሸናፊ ነውም ብለዋል፡፡
በታርቆ ክንዴ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/