ባሕር ዳር: ጥቅምት 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገርህ ናት በከፍታም በዝቅታም ዘመን አስባት፣ ሀገርህ ናት በደምህ ጠብቃት፣ በአጥንትህ አስከብራት፣ ሀገርህ ናት በክብሯ ላይ የሚነሱትን ቅጣላት፣ በአሸናፊነት አኑራት፡፡ ለሀገር የቆሙትን አስባቸው፣ ለሀገር ሕይወት የሚሰጡትን ጠብቃቸው፣ አክብራቸው፣ ከፍ ከፍም አድርጋቸው፡፡ ሀገር ሲከፋ የምትረሳ፣ ሲደላ የምትነሳ፣ በመከራ ዘመን የሚተዋት፣ በፍስሃ ዘመን የሚያስቧት፣ የሚያስታውሷት አይደለችም፣ ሀገር በመከራም በፍስሃም ዘመን የሚያስቧት፣ የማይረሷት፣ የሚጠብቋት፣ ከነብስ በላይ የሚያከብሯት ናት እንጂ፡፡
ጀግኖች ስለ ሀገር ሞትን ንቀዋል፣ ስለ ሀገር ምቾት ረስተዋል፣ ስለ ሀገር ድንጋይ ተንተርሰው፣ ጤዛ ልሰው ኖረዋል፣ ስለ ሀገር ተጠምተዋል፣ ስለ ሀገር ተርበዋል፣ ስለ ሀገር እንቅልፍ አጥተዋል፡፡ አበው ሲመርቁ የምትኖርበት ሀገር አያሳጣህ፣ የምትኮራበት ሠንደቅ አይንሳህ ይላሉ፡፡ ሀገር የተሰጠው፣ ሠንደቅ ያልተነሳው ሰው የተመረጠ ነውና፡፡
ብዙዎች የሚኮሩበት ሀገር አጥተው፣ ሠንደቃቸውን ተነጥቀው በባዕዳን ሀገር በግፍ ኖረዋል፣ በባርነት ተሰቃይተዋል፣ ሲከፋቸው የሚመለሱባት ሀገር፣ የሚያውለበልቧት ሠንደቅ የላቸውምና የተጫነባቸውን ሸክም ተሸክመዋል፣ በባርነት ሠንሰለት ውስጥ ታስረው ኖረዋል፡፡ ሀገር ያላቸው ባርነትን አይቀበሉም፣ ሀገር ያላቸው በመገፋት ውስጥ አይኖሩም፣ ሀገር ያላቸው በግፍ አይገብሩም፣ በመከራ ሠንሰለት አይታሠሩም፡፡
ለባርነት እጅ የማይሰጡት፣ የጨለማውን ዘመን የሚያርቁት ጀግኖች ሀገር ሊያሳጣቸው የተነሳውን ሁሉ እየቀጡ መልሰውታል፣ ከጉልበታቸው በታች አድርገው አንበርክከውታል፣ ኢትዮጵያውያን በየዘመናቱ ሀገር ሊያሳጣቸው፣ ሠንደቅ አልባ ሊያደርጋቸው የተነሳው ጠላት እልፍ ነው፡፡ ዳሩ ለአንደኛውም አንገታቸውን አልደፉም፣ ክብራቸውን አላስደፈሩም፣ በኢትዮጵያ ሠማይ ሥር በሀገርና በሠንደቅ ቀልድ የለም፡፡ ሠንደቋን የተዳፈረውን ይመቱታል፣ ሀገር የነካውን ይጥሉታል እንጂ፡፡
ሠንደቅ ይከበራል፣ ሠንደቅ ከጉዞ ይቀድማል፣ ለሠንደቅ ከሕይዎት በላይ ክብር ይሰጣል፣ ለአረንጓዴ፣ ቢጫ ቀዩ ሠንደቅ ክብርና ፍቅር እልፍ የመከራ ዘመኖች ታልፈዋል፡፡ ኢትዮጵያዊ ሠንደቁን ያከብራል፣ ሠንደቁን ያስከብራል፣ በሠንደቁ ይከብራል፣ በቀደመው ዘመን ስለ ሠንደቁ ብለህ ተነስ የተባለ ሁሉ እንደ አይን ጥቅሻ እንደ ከንፈር ንክሻ ፈጥኖ ይነሳል፣ ሠንደቁ ተደፈረ፣ ድንበር ተሰረሰረ ወደ ተባለበት ሥፍራ ይገሰግሳል፡፡ በሠንደቁ ስም ብቻ ይዘምታሉ፣ በሠንደቁ ምለው ይመታሉ፣ በሠንደቁ ፎክረው ይጥላሉ፣ በሠንደቁ ደምቀው ይገሰግሳሉ፡፡
በሠንደቁ አምላክ የተባለው እጁን ለጥል አያነሳም፣ በደሎች ቢበዙበትም፣ እልህ ቢተናነቀውም በሠንደቁ አምላክ ከተባለ ለግድያ ያነሳውን ጎራዴውን ወደ ሰገባው ይመልሳል፣ ሳንጃውን ይነቅላል፣ አፈሙዙን ያዞራል፡፡ ለምን የሠንደቁ ስም ተጠርቷልና፡፡
አረንጓዴ፣ ቢጫ ቀዩዋ ሠንደቅ ተስፋ ናት ቃል ኪዳን የተሰጠባት፣ የመከራው ዘመን የታለፈባት፣ ጠላት የተረታባት፣ ወገን የበረታባት፣ ከፊት አስቀድሞ የከፋውን ዘመን የተሻገሩባት፣ ክብር ናት ደምና አጥንት የተከፈለባት፣ መለያ ናት ኃያልነት ያደመቃት፣ ጠላት የሚፈራት፣ በአሻገር የሚሰግድላት፡፡
የኢትዮጵያ ሠንደቅ ኃያላን ነን ከሚሉት በላይ ከፍ ብላ ተውለብልባለች፣ በጠላት ሠፈር በአሸናፊነት ከፍ ብላ ታይታለች፣ ለጥቁሮች ምልክት ኾናለች፣ ተስፋ ኾና በሰማይ ላይ ታይታለች፡፡ አሸናፊ ተብላ በማይጠፋ መዝገብ ላይ ተመዝግባለች፡፡ በሠንደቋ ቃል ኪዳን ተሰጥቷል፣ በሠንደቋ ድል ተነስቷል፣ በሠንደቋ የጨለመው በርቷል፣ የከበደው ቀልሏል፣ የደበዘዘው ጎልቷል፡፡
የኢትዮጵያ ጀግኖች ለእናታቸው ለኢትዮጵያ ክብር፣ ለመመኪያቸው፣ ለምልክታቸው፣ ለመኩሪያቸው ለሠንደቃቸው ፍቅር ሲሉ በባዶ እግር ተጉዘዋል፣ በዱር በገደል ተንከራትተዋል፣ ከልጆቻቸው ርቀው ተዋድቀዋል፡፡ በሞታቸው አኑረዋታል፣ በደማቸው አጽንተዋል፣ በአጥንታቸው አስከብረዋታል፡፡ የኢትዮጵያ ጀግና ከጠላቱ ጋር በገጠመ ጊዜ የጠላቴ ጥይት ጀርባዬን ከመታኝ ስሸሽ ነውና የተመታሁት አትቅበሩኝ፣ በወደቅሁበት ተውኝ፣ አሞራ ይብላኝ፣ አራዊት ይጫወትብኝ፡፡ ለሀገሬ ስዋጋ በፊቴ ከተመታሁ ግን የጀግና ክብሩ በጀግንነት መሞቱ፣ በጀግንነት መሰዋቱ ነውና በክብር ቅበሩኝ፣ አስከሬኔን አረንጓዴ፣ ቢጫ ቀዩዋን ሠንደቅ አልብሱልኝ፣ ስለ እርሷ ስል ነውና የወደቅሁት በእርሷ ጠቅልላችሁ ሸኙኝ፣ የእናት ሀገሬን አፈር አቅምሱኝ ይላል፡፡ ኢትዮጵያዊ ጀግና ሠንደቁ ሲኖር የሚያጌጥባት፣ ከምንም በላይ የሚያስቀድማት ሲሞት የሚከፈንባት፣ ተውቦ የሚያርፍባት ናት፡፡
ቃል ሰጥቶ ቃል ይቀበላል፣ እየሰገረ ሄዶ ጠላቱን ይደመስሳል፣ ሠንደቁን በጠላት መቃብር ላይ ከፍ አድርጎ ያውለበልባል፣ ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ እያለ ይጣራል፡፡
እልፍ ጠላቶች በሠንደቋ ላይ ይነሳሉ፣ በእልፍ ጀግኖች ተመትተው ይወድቃሉ፣ እልፍ ጠላቶች በኢትዮጵያ ላይ ይዘምታሉ፣ በክንደ ብርቱ ጀግኖች ተሰብረው ይቀራሉ፣ ወደ መጡበት ሳይመለሱ ለዘላለም ያሸልባሉ፡፡ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩዋ ሠንደቅ በኩራት የተውለበለበችው፣ ኢትዮጵያ በጽናት የኖረችው ዝም ብሎ አይደለም፡፡ ደም ፈስሶ፣ አጥንት ተከስክሶ፣ ሕይዎት ተገብሮ ነው እንጂ፡፡
በደም ቃል ኪዳን የተረከቧት፣ ከጉልበታቸው ሸብረክ ብለው፣ እጅ ነስተው የተቀበሏት የኢትዮጵያ ጀግኖች አባቶቻቸውና እናቶቻቸው በደምና በአጥንት እንዳስከበሯት፣ በሕይዎት መስዋእትነት እንዳኖሯት እነርሱም በደምና በአጥንት ሊያኖሯት ምሽግ ውለው ምሽግ እያደሩ እየተዋደቁላት ነው፡፡
ʺለኔ ለኔ ሳንል ለአንድነቷ ቆመን
ኢትዮጵያን እናንሳ ከሁሉ አስቀድመን” እንደተባለ ከሁሉ አስቀድመን ኢትዮጵያን እናንሳ፣ ከሁሉ አስቀድመን ኢትዮጵያን እናውሳ፣ ከሁሉ አስቀድመን ለኢትዮጵያ እንነሳ፡፡ ኢትዮጵያን ያሉት እንጂ ለኔ ያሉት አላሸነፉም፣ ኢትዮጵያን ያሉት እንጂ ለኔ ያሉት መከራውን አላለፉም፣ ኢትዮጵያን ያሉት እንጂ ለኔ ያሉት በደማቅ ብዕር፣ በማያረጅ ብራና አልተጻፉም፡፡ ለኔ ማለት ከፍታ አይደለም፣ ለኔ ማለት ዝቅታ ነው፡፡
ለኔ ለኔ ያሉት ተረስተዋል፣ ለኔ ለኔ ያሉት በትውልድ ተወግዘዋል፣ በታሪክ መዝገብ ላይ ተዘለዋል፣ ኢትዮጵያ መመኪያ ናትና ከሁሉ እናስቀድማት፣ ኢትዮጵያ መከበሪያ ናትና እናክብራት፣ እናስከብራት፣ ኢትዮጵያ ምስጢር ናትና ምስጢሯን እንያዝላት፣ እንጠብቃት፣ ኢትዮጵያ ቅኔ ናትና ቅኔዋን እንፍታላት፣ ኢትዮጵያ ለጨለመባቸው መብራት ናትና ከፍ አድርገን በዓለሙ ሁሉ እናብራት፡፡
የመከራው ዘመን የታለፈባትን፣ ጥቁር ሁሉ ነፃ የወጣባትን ፣ነጭ ሁሉ የተንበረከከባትን፣ በአሻገር ኾኖ የደነገጠባትን፣ የተስፋ ዘንባባ የመጣባትን፣ ቃል ኪዳን የታሰረባትን፣ በረከት የሚመጣባትን ሠንደቅ አብዝተህ ጠብቃት፣ አክብረህ ተከበርባት፣ ጠላቶቿን መትተህ ድመቅባት፡፡
ኢትዮጵያን ብለህ ተነስና ኢትዮጵያ እንደማትሸነፍ አሳያቸው፣ እማማ ብለህ ገሰግስና በኢትዮጵያ ላይ እግራቸውን የሚያነሱትን አሳፍራቸው፡፡ ኢትዮጵያን ብለው የተነሱትን ተከተላቸው፣ ኢትዮጵያን ብለው የተነሱትን ጋሻ ሁናቸው፣ ኢትዮጵያን ብለው የተነሱትን አክብራቸው ደጀንና አለኝታ ሁናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በደም ቃል ኪዳን እንደተሰጠችህ ሁሉ በደምና በአጥንት አስከብረህ አኑራት፡፡ ከምንም በላይ ከፍ ከፍ አድርጋት፣ ለምን ካሉ እርሷ ካለች ሁሉም አለ፣ እርሷ ከሌለች ሁሉም የለምና፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለሀገር ክብር በትግል እናብር!!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J